Search

ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያ ተአምራቱን የሰራበት እለት "ቃና ዘገሊላ" በድምቀት እየተከበረ ነው

ማክሰኞ ጥር 12, 2018 415

በየዓመቱ የጥምቀት በዓል በዋለ በማግስቱ የሚከበረው "የቃና ዘገሊላ" በዓል ዘንድሮም በተለየያዩ አካባቢዎች በድምቀት እየተከበረ ነው።

እንደ ኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን አስተምህሮ የጥር ወር የውኃ በዓላት የሚበዙበት ወር ከመሆኑም ባሻገር "ዘመነ መርዓዊ" (የሙሽራ ዘመን) ይባላል፡፡ የውኃ በዓል የተባለበት ምክንያት ጥምቀት እና ቃና ዘገሊላ የውኃ በዓላት በመሆናቸው ሲሆን፣ "ዘመነ መርዓዊ" የተባለው ደግሞ በቃና ዘገሊላ ሠርግ ቤት በኢየሱስ ክርስቶስ የተፈፀመውን የመጀመሪያ ተአምር በማስመልከት ነው፡፡ ከዚህ ጋርም ተያይዞ ወሩ ሠርግ የሚበዛበት ወርም ነው፡፡

"ቃና ዘገሊላ" በቀጥታ ትርጉም ገሊላ የምትገኘው የቃና መንደር ማለት ሲሆን እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን አስተምህሮ በጥምቀት በዓል ማግስት (ጥር 12) ቀን የቃና ዘገሊላ በዓል ይከበራል፡፡

ይህ በዓል ከክርስቶስ ጥምቀት በዓል ጋር ተያይዞ በድምቀት የሚከበር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዳራ ያለው በዓል ነው፡፡ በዓሉ ቃና ዘገሊላ የሚል ስያሜ ያገኘው ኢየሱስ ክርስቶስ የገሊላ ሀገር ክፍል በምትሆን ቃና በተባለችው ቦታ በፈፀመው ተአምር መነሻነት እንደሆነ የቤተክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ያስተምራሉ፡፡ 

በዚህ ቃና በተባለ ቦታ ኢየሱስ ክርስቶ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም እና ከሐዋርያቱ ጋር ወደ ሠርግ ቤት ሄዶ፤ በሰርግ ቤቱ የነበረው የወይን ጠጅ በማለቁ ምክንያት ውሃውን ወደ ወይን በመቀየር የመጀመሪያ ተአምራቱን በማድረጉ የሚከበር በዓል ነው፡፡ 

እንደ ሃይማኖቱ አባቶች አስተምህሮ የቃና ዘገሊላ ተአምር የተፈፀመው የካቲት 23 ቀን ቢሆንም ጥምቀት የውኃ በዓል በመሆኑ "የውኃን በዓል ከውኃ በዓል ጋር ማክበር ይገባል" ብለው የየካቲቱን በዓል ወደ ጥር 12 እንዳመጡት ይነገራል፡፡

የካቲት 23 የፆም ወቅት በመሆኑ ጭምር በዚህ ወቅት የኢየሱስ ክርስቶስን መከራ የሚታሰብበት እንጂ የደስታ ጊዜ ባለመሆኑ ከሚስማማው ወቅት ጋር እንዲከበር መደረጉን መምህራን ያስተምራሉ።

ይህም ውኃ ወደ ወይን የተለወጠበትን ዕለት ከክርስቶስ በውኃ ከተጠመቀው የጥምቀት በዓል ጋር ለማስተሣሠር በማሰብ የቃና ዘገሊላ በዓል የጥምቀት በዓል ማግስት ጥር 12 ቀን ይከበራል፡፡ 

ከቃና ዘገሊላ ጋር በከተራ ዕለት ወደ ወንዝ የሚወርደው የቅዱስ ሚካኤል ታቦት በጥምቀት ዕለት (ጥር 11) ወደ ደብሩ ስለማይመለስ ባደረበት ቦታ የቃና ዘገሊላ ማህሌት እና ቅዳሴ ተፈጽሞ፣ መዝሙራት ተዘምረው ታቦታ ሕጉ ወደ መንበሩ ይመለሳል፡፡