Search

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) መካከል የተደረገውን የዘላቂ ሰላም ስምምነት ማዕቀፍ ውጤታማ ለማድረግ የማስፈፀሚያ ስምምነት ተፈረመ

ሓሙስ ጥር 14, 2018 353

ስምምነቱን አስመልክቶ በተካሄደው መድረክ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አመራሮች፣ የሰላም ሚኒስቴር፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አመራሮች እንዲሁም በመንግስት የቀረበውን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ የአፋህድ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
በስምምነቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የሰላም ሚኒስትሩ መሀመድ እድሪስ በክልልሉ የነበረው ግጭት ከፍተኛ ውድመትን ያስከተለ ነው፤ ይህም ህዝባችን ሊያገኝ የሚገባውን የሰላምና የልማት ያሉ ሰብአዊ መብቶችን አሳጥቷል ብለዋል።
በዚህ በሰለጠነ ዘመን ከሰላም ይልቅ አፈ ሙዝ ይዞ መፉተግ ጊዜውን የማይመጥን እና በትውልድ ተወቃሽ የሚያደርግ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ሰላምን መርጠው ወደ ሰላም መንገድ የመጡት የአፋሕድ አመራሮች ተገቢውን እና ለትውልድ የሚበጅ ውሳኔ በመምረጣቸው ምስጋና ችረው፣ ሌሎች ቀሪ ኃይሎችም የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የአፋሕድ ከፍተኛ አመራር ኮለኔል ፈንታው ሙሀባ በበኩላቸው፣ ስምምነቱን ባለፉት ጊዜያት በአፍሪካ ኅብረት እና በኢጋድ አማካኝነት በሕጋዊ መንገድ ውይይት ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል።
ስምምነቱ ያለፈውን የሚያጠናክር እና ሕጋዊ በሆነ መልኩ የተፈፀመ መሆኑን ገለጸው፣ “ባለፈው ጦርነት የአማራ ሕዝብ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት የዐይን እማኝ ነን፤ ክልሉም ከዚህ በላይ ጦርነት የመሸከም አቅም የለውም” ብለዋል።
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) መካከል የዘላቂ ሰላም ስምምነት ኅዳር 25 2018 ዓ.ም መፈረሙ ይታወሳል።
በዛሬው ዕለት የተፈረመው ስምምነትም የዘላቂ ሰላም ስምምነቱን ማእቀፍ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ማስፈፀሚያ ነጥቦችን የያዘ ነው።
ስምምነቱንም የአማራ ክልል የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር) እና የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) ወታደራዊ አስተዳደር አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ኢያሱ አባተ ተፈራርመዋል።
በጌታቸው ባልቻ