Search

በኢትዮጵያ እና በሦስት የብሪክስ አባል ሀገራት መካከል ፍርደኞችን ማስተላለፍ እንዲሁም የወንጀል ጉዳይ የአሳልፎ መስጠት አዋጆች ፀደቁ

ሓሙስ ጥር 14, 2018 274

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባዔው፣ ከሦስት የብሪክስ አባል ሀገራት ጋር በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የሕግ ትብብር እንዲሁም ፍርደኞችን ለማስተላለፍ የስምምነት አዋጆችን አፅደቋል።
ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ እና ቻይና መንግሥት መካከል የተደረገውን የወንጀል ጉዳዮች የጋራ የሕግ ትብብር ስምምነት ረቂቅ አዋጅ እና በሁለቱ መንግሥታት መካከል የተደረገውን ፍርደኞችን የማስተላለፍ ስምምነት ረቂቅ አዋጅ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።
በኢትዮጵያ እና በብራዚል መንግሥት መካከል የተደረገውን ፍርደኞችን የማስተላለፍ ስምምነት ረቂቅ አዋጅ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።
እንዲሁም በኢትዮጵያ መንግሥት እና በደቡብ አፍሪካ መንግሥት መካከል የተደረገውን በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት ረቂቅ አዋጅን በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።
በምክር ቤቱ የሕግ እና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ እፀገነት መንግሥቱ የረቂቅ አዋጆቹን ሪፖርት እና የውሳኔ ሀሳብ ባቀረቡበት ወቅት በኢትዮጵያ እና በሦስቱ የብሪክስ አባል ሀገራት መካከል እያደገ የመጣውን ግንኙነት በሕግ ማስደገፍ ለግንኙነቱ መጠናከር የሚኖረውን አስተዋፅኦ ተናግረዋል።
በተለይም ወንጀልን በጋራ ለመከላከል እንዲሁም ፍርደኞች በራሳቸው ሀገር እና ማኅበረሰብ ፍርዳቸውን እንዲከታተሉ የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው ሕጉን ለማስፈፀም በተለይም በኢትዮጵያ እና ቻይና መንግሥት የኃይል ልዩነት መኖሩ ተፈፃሚነት ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ በስጋትነት አንሥተዋል።
እንዲሁም በብራዚል ሀገር ኢትዮጵያዊያን ፍርደኞች ስለመኖራቸው ጥያቄ ያነሡ አንድ የምክር ቤት አባል የሕጉ አስፈላጊነት ተቃውመውታል።
በተጨማሪም ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ እና በኮሪያ ኤክስፖርት-ኢምፖርት ባንክ መካከል ለሕክምና መሣሪያዎች አቅርቦት ፕሮጀክት ምዕራፍ 2 ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጅ፣ የኅብረት ሥራ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ፣ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ሴኩዩሪቲ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን እና የፌዴራል የስፖርት ልማት እና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች በመምራት ጉባዔው ተጠናቋል።
በሞላ ዓለማየሁ