የኢትዮጵያ አየር መንገድን በሎሜ፣ ሉሳካ እና ሊሎንግዌ አዳዲስ መዳረሻዎችን በመክፈት አህጉሪቱን እያስተሳሰረ እንደሚገኝና የአፍሪካ ኩራት መሆኑን በተግባር እያረጋገጠ መሆኑን ፕሮፌሰር ጆሴፍ ገለጹ።
አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ ደረጃም ወደ ፊሊፒንስ እና ጄኔቫ የመሳሰሉ አዳዲስ መዳረሻዎችን በማስፋት ስትራቴጂካዊ ጉዞውን አጠናክሮ መቀጠሉንም ፕሮፌሰሩ አንስተዋል።
ጋናዊው ፕሮፌሰር ከኢቲቪ "አዲስ ዳያሎግ" ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፣ መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉ የፈጠራ ክህሎት የተሞላባቸው እና የረጅም ጊዜ እርምጃዎች ቦታን እና ጊዜን ለማቀራረብ የሚረዱ ናቸው። ለዚህም በ12.5 ቢሊዮን ዶላር የሚገነባውን የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት እንደ ዋና ማሳያ ጠቅሰውታል። ፕሮጀክቱ ለአፍሪካ ትሥሥር ትልቅ ለውጥ ከማምጣቱም ባሻገር፣ ለበርካታ ዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ለኢኮኖሚው ትልቅ አቅም እንደሚሆንም ምሁሩ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ችግሮች ሲፈጠሩ ብቻ ምላሽ ከመስጠት ወጥቶ፣ ለረጅም ጊዜ የሚዘልቁ ስትራቴጂካዊ ዕቅዶች ላይ ማተኮሩ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግር የሚደነቅ እርምጃ መሆኑን የዮርክ ዩኒቨርሲቲ ምሁር ፕሮፌሰር ጆሴፍ ሜንሳህ ገለጹ።
ኢትዮጵያ እያደረገችው ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በተመለከተ አስተያየታቸውን የሰጡት ፕሮፌሰሩ፣ ማንኛውም ሪፎርም "የፈጠራ እና የውድመት ባህሪ" እንዳለው ጠቁመው፣ አዲሱን ሥርዓት ለመፍጠር የድሮውን መዋቅር ማደስ ግድ እንደሚል አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ወጣቶች ለሀገሪቱ ቀጣይ ሁለት አሥርት ዓመታት ትልቁ ሃብት መሆናቸውን ምሁሩ አጽንኦት ሰጥተውበታል። ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት አንፃር ብዛት ያለው ወጣት ትውልድ ያላት በመሆኑ፣ ይህንን አቅም በአግባቡ ለመጠቀም ኢኮኖሚው በቂ የሥራ ዕድል መፍጠር እንዳለበት አመላክተዋል። ፕሮፌሰር ሜንሳህ አክለውም ኢትዮጵያ የጀመረችው ስትራቴጂካዊ እርምጃ ቦታን እና ጊዜን በማቀራረብ ረገድ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እየከፈተ መሆኑን ገልጸዋል።
በላሉ ኢታላ