ለዘጠኝ አስርት ዓመታት በጀግንነት ታንፆ ለሀገር ሉዓላዊነት ዘብ የቆመው የኢትዮጵያ አየር ኃይል፣ የትውልድ ቅብብሎሽን በተግባር እያሳየ ይገኛል።
አየር ኃይሉ የሀገርን አደራ በመሸከም ለዛሬው ኩራትና ግርማ የበቃው በአባላቱ ቁርጠኝነትና በማይበጠስ የመተካካት መንፈስ ነው።
ኢቢሲ በዚህ የትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ አርአያ የሚሆኑና በኢትዮጵያ አየር ኃይልውስጥ እያገለገሉ የሚገኙ አባትና ልጅን አነጋግሯል።
በአቪዬሽን ጥገና ማዕከል ውስጥ ለ28 ዓመታት በታማኝነት ያገለገሉት ሻለቃ አንተነህ ካሳ፤ ሀገር የምትቀጥለው በትውልድ ቅብብሎሽ መሆኑን ይናገራሉ።
ልጃቸው የአየር ኃይሉን ዩኒፎርም ለብሶ ለሀገሩ ዘብ ሲቆም በማየታቸው የተሰማቸውን ጥልቅ ኩራት ገልጸዋል።
"ሀገርን ማገልገል ትልቅ ክብር የሚሰጠው ተግባር ነው፤ ልጄ የእኔን ፈለግ ተከትሎ ሀገሩን ለማገልገል በመፈለጉ ትልቅ ኩራት ይሰማኛል" ብለዋል፡፡
ሻለቃ አንተነህ አክለውም፤ በአየር ኃይል ውስጥ የሚገኘው የዓላማ ፅናት፣ ችግሮችን የመቋቋም ብቃት እና በራስ መተማመን ለማንኛውም ወጣት ትልቅ የአቅም ግንባታና የሕይወት ትምህርት መሆኑን አስገንዝበዋል።
የአባቱን ፈለግ የተከተለው መሰረታዊ ወታደር ወጣት ዮናስ አንተነህ፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ አየር ኃይል አካዳሚ የቤዚክ አቪዬሽን ተማሪ ሲሆን የ6 ወራት ስልጠናውን አጠናቋል።
ወጣት ዮናስ ለአየር ኃይል ሙያ ፍቅር እንዲያድርበት ያደረገው የአባቱ ቆራጥነት፣ ሞራልና ሥነ-ምግባር መሆኑን ይገልጻል።
ወጣቱ በስልጠና ቆይታውም ወታደራዊ ሥነ-ምግባርን፣ ለዓላማ በፅናት መቆምን እና አንድ ወታደር ሊኖረው የሚገባውን ጥንካሬ ከአባቱም ሆነ ከተቋሙ ማግኘቱን ተናግሯል።
በዘመናዊ ትጥቅና በሰለጠነ የሰው ኃይል ራሱን እያጠናከረ ያለው የኢትዮጵያ አየር ኃይል፤ ይህን መሰል የአባትና ልጅ የሙያ ቅብብሎሽ ለተቋሙ ቀጣይነትና ለሀገር ተስፋ ትልቅ መሰረት ነው።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ