"የኢትዮጵያ አየር ኃይል የነፃነትና የአንድነት ምልክት" በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን 90ኛውን የአየር ኃይል ቀንን በማስመልከት ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ከተወጣጡ የአየር ኃይል አዛዦች፣ ወታደራዊ አታሼዎች፣ የወታደራዊ አቭዬሽን ትጥቅ አምራች ኩባንያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የጋራ ሥራዎቻችንን አጠናክረን የተረጋጋ አለምን እንገባ በሚል መሪ ሐሳብ ሦስተኛው 2026 የአፍሪካ አየር ኃይል ፎረም በቢሾፍቱ ከተማ ሆራርሰዴ አዳራሽ ተካሂዷል።

የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በፎረሙ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፣ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የመላው አፍሪካዊያን ኩራት ነው ብለዋል።
የሰው ዘር መገኛ፣ የነፃነት እና የድል አድራጊነት ተምሳሌት ለመላው ጥቁር ህዝቦች የኩራት ምንጭ ወደሆነችው ቀደምት ሀገር ኢትዮጵያ እንኳን በደህና መጣችሁ ብለዋል ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል በአይበገሬነት፣ በድል አድራጊነትና የጠላትን የማድረግ አቅም በማደባየት በዘመናት መካከል ኢትዮጵያን በማፅናት የታላቅ ሀገር ታላቅ ተቋም መሆን ከመቻሉም በላይ ከኮንጎው የሰላም ተልዕኮ አንስቶ በሩዋንዳ፣ ሱዳን ሶማሊያና ሌሎች የሰላም ማስከበር ግዳጆች ላይ በመሳተፍ የመላ አፍሪካዊያን ኩራት መሆኑን ያረጋገጠ ታላቅ ተቋም እንደሆነም ተናግረዋል።
በ1928 ሻለቃ ሚሽካ ባቢቼፍን ዋና አዛዥ በማድረግ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም የአቭዬሽን ተቋም ሆኖ የተመሰረተው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ምንም እንኳን በበርካታ ውጣ ውረዶችና ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ቢያልፍም በዘመናት መካከል እየደመቀ ከሶማሌያው ዚያድባሬ ጀምሮ እስከ አሸባሪው አልሸባብ ድረስ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመዳፈር የቋመጡ የውጭ ወራሪዎችንና ሽብርተኞችን ድባቅ እየመታ እና በድል እያሸበረቀ ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገር ደማቅ የ90 ዓመታት ታሪክ መፃፍ የቻለ ታላቅ ተቋም ነው ብለዋል።
ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በተለይም ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ መንግስት ለአየር ኃይል በሰጠው ልዩ ትኩረት በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በሰው ኃይል ግንባታ፣ በውጊያ መሠረት ልማትና ሌሎች በርካታ የሪፎርም ስራዎችን በመስራት ላለፉት 8 አመታት የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥን አየር ኃይል ለመገንባት ሥራዎችን መስራት በመቻሉ ተቋሙ አመርቂ ስኬት እያስመዘገበ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በመጨረሻም ዋና አዛዡ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የነፃነትና የአንድነት ምልክት በመሆን ለአፍሪካዊያን የጋራ ዕድገት እና አንድነት በትኩረት የሚሰራ መሆኑን መናገራቸውን ከመከላከያ ሠራዊት የማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በፎረሙ ላይ የተለያዩ የአቭዬሽን ትጥቅ አምራች ኩባንያዎች ስለ አለም የአቭዬሽን ቴክኖሎጂ ዕድገትና ስለሚያመርቷቸው ዘመናዊ ትጥቆች ሰፊ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን የአፍሪካ ሀገራት አየር ኃይል አዛዦችም በፎረሙ ላይ የተለያዩ ሀሳቦችን በመስጠት ለኢትዮጵያዊያን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።