Search

የ90 ዓመታት የሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት የማስጠበቅ ጉዞ - የኢፌዴሪ አየር ኃይል

ዓርብ ጥር 15, 2018 380

በዓለም ላይ የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ በተጀመረ በ17ኛው ዓመት ማለትም በ1912 ዓ.ም ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂውን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ከአፍሪካ ቀዳሚ መሆኗን የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ።

ይህ ታሪክ ኢትዮጵያ ሥልጣኔን ቀድማ የመላመድ ፍላጎቷን እና የነበራትን ታላቅነት የሚያሳይ ሲሆን፣ በይፋ በ1921 ዓ.ም የመጀመሪያው አውሮፕላን በኢትዮጵያ ምድር ሲያርፍ የአቪዬሽን ልደት በደመቀ ሁኔታ ተበስሯል።

የታሪክ ከፍታ እና ዝቅታዎች የኢትዮጵያ አየር ኃይል በ1928 ዓ.ም አየር ኃይል የሚል ስያሜ ይዞ ተቋማዊ አደረጃጀቱን ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ በርካታ ታሪካዊ ምዕራፎችን አሳልፏል።

በንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የምዕራባውያንን በተለይም የአሜሪካን ትጥቆች በስፋት በመታጠቅ የወርቃማ ዘመኑን አሳልፏል።

በወቅቱም በኦጋዴን በኩል የተነሣውን የሶማሊያ ወረራ በማክሸፍ እና በኮንጎ ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በመሳተፍ ደማቅ ታሪክ አስመዝግቧል።

ከደርግ መንግሥት መምጣት በኋላ ተቋሙ ወደ ሶቪየት ኅብረት ትጥቆች ማለትም ከሚግ 21 እስከ 23 ጄቶች በመዞር አቅሙን ገንብቷል።

በተለይም በ1969/70 ዓ.ም በካራማራ ተራሮች ላይ ከ25 በላይ የጠላት ጄቶችን በመደምሰስ ያስመዘገበው ድል በአየር ኃይሉ ታሪክ በወርቅ ቀለም የተጻፈ ገድል ነው።

ይሁን እንጂ ከደርግ ውድቀት በኋላ ተቋሙ በአዲሱ መንግሥት ዘንድ "አየር ኃይል አያስፈልግም" በሚል የተዛባ አመለካከት አብራሪዎቹ ተበታትነው እና ተቋሙ ፈርሶ የቁልቁለት ጉዞውን ጀምሮ ነበር።

የዳግም ትንሣኤ እና የዘመናዊነት ጉዞ ከ2010 ዓ.ም የለውጥ መንግሥት መምጣት በኋላ፣ አየር ኃይሉ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ብቁ እንዲሆን ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል። በወቅቱ ተቋሙ በማርጀት እና ተዋጊ ጄቶች በማጣት የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበት የነበረ ቢሆንም፣ ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ ተቋሙን ከፖለቲካ፣ ከሃይማኖት እና ከብሔር ወገንተኝነት በማላቀቅ የዘመኑን ቴክኖሎጂ የታጠቀ ኃይል መገንባት ተችሏል።

የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ እንደሚሉት፣ ተቋሙ አሁን ላይ ሲስተሙን ከአናሎግ ወደ ዲጂታል በመቀየር፣ ዘመናዊ የውጊያ አውሮፕላኖችን በመታጠቅ እና የጥገና ባለሙያዎችን በራሱ በማፍራት የላቀ ደረጃ ላይ ደርሷል።

በተለይም ለውጊያ የሚሆኑ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮኖችን) ማምረቻ ማዕከል መገንባቱ እና አምና "ፀሐይ 2" አውሮፕላንን በሀገር ውስጥ አቅም መገጣጠም መቻሉ የአየር ኃይሉን የከፍታ ጉዞ ማሳያ ናቸው።

የወደፊት ራዕይ የኢፌዴሪ አየር ኃይል በ2022 ዓ.ም (እ.ኤ.አ በ2030) ተቋሙን ከአፍሪካ ቀዳሚ ለማድረግ ራዕይ ሰንቆ እየሠራ ይገኛል።

ባለፉት 90 ዓመታት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ሲያስጠብቅ የኖረው ይህ አንጋፋ ተቋም፣ ዛሬም በቴክኖሎጂ ዘምኖ የሀገራችንን ሰማይ 24 ሰዓት በተጠንቀቅ በመጠበቅ ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል 90ኛው ዓመት የምስረታ በዓል እንኳን አደረሳችሁ!

በቶማስ ኃይሉ