Search

የወል ትርክት ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ

ቅዳሜ ጥር 16, 2018 288

ኢትዮጵያውያን በአንድነት በሚያስተሣሥራቸው የጋራ ዕሴቶቻቸው እና ባህሎቻቸው ለረጅም ዘመናት እርስ በእርስ በመከባበር እና በመተሳሰብ ኖረዋል።

ሆኖም በመሐል የተፈጠሩ ነጣጣይ ትርክቶች ሀገር እና ሕዝብን ለግጭት እና ለክፍፍል ሲዳርጉ ቆይተዋል።

የነጠላ ትርክት ስብራትን መጠገን ለአንድ ሀገር ዕድገት እና ሰላም መስፈን ትልቅ ሚና ያለው በመሆኑም በመደመር መንግሥት ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ይገኛል።

የአፋር ዳያስፖራ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገአስ አሕመድ፤ ለአንዲት ሀገር ልዩነትን የሚያከብር የጋራ ታሪካዊ ዕሴቶችን መገንባት መሠረታዊ ጉዳይ ነው ይላሉ።

አቶ ገአስ አሕመድ ከኢቲቪ አዲስ ቀን መሰናዶ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ከዚህ በፊት የነበሩ ነጣጣይ ትርክቶች ለግጭት እና ለመከፋፈል አመቺ እንደነበሩ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ የተጋመደ እና የማይለያይ ማንነት ያለን ሕዝቦች ነን ያሉት ኃላፊው፣ ጠንካራ ሀገርን ለመገንባት የወል ትርክት ወሳኝ መሆኑን አስምረውበታል።

ልዩነት ውበት እንጂ ለመከፋፈል እና ለግጭት ምክንያት መሆን እንደማይገባውም አንሥተዋል።

የነጣጣይ ትርክት መጨረሻ ሀገርን ማፍረስ መሆኑን እነ ሶሪያ እና ሊቢያ ምስክር መሆናቸውን ጠቁመው፣ ነጣጣይ እና የሚለያዩ ጉዳዮችን ወደ ጎን በመተው አንድነታችን ላይ ማተኮር አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው ብለዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና ተመራማሪ አቶ ካሚል መሐመድ በበኩላቸው፣ ነጣጣይ ትርክት ሊለያየን እና ሀገርን ሊያፈርስ የሚችል አንደሆነ ገልጸው፣ ሁሉንም ያቀፈ የወል ትርክት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያን ለጋራ ዓላማ በአንድነት ስንቆም የማናሳከው ነገር እንደሌለ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ስኬት ኅያው ምስክር መሆኑንም አንሥተዋል።

ፈተና ከሆነብን የነጠላ ትርክት ወደ ኅብረ-ብሔራዊ ትርክት ለመሸጋገር ባለፉት የለውጥ ዓመታት አሳታፊ ሥራዎች መከናወናቸውንም አቶ ካሚል ገልጸዋል።

በሜሮን ንብረት

#Ebc #Ebcdotstream #Ethiopia #Unity #ኅብረ_ብሔራዊት_ኢትዮጵያ