የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢፌዴሪ አየር ኃይልን 90ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን በማስመልከት በትናንትናው ዕለት በተዘጋጀው የጥቁር አንበሳ የአየር ላይ ትርዒት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ "ወዳጅም ጠላትም አንድ እንዲገነዘብ የምንፈልገው ነገር ኢትዮጵያ ከምታውቋት ያለፈች ሀገር መሆኗን ነው" ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለወዳጆቿ በሯን ከፍታ በትብብር ለመሥራት እና አብሮ ለማደግ ዝግጁ መሆኗን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይሁን እንጂ ብሔራዊ ጥቅሟን ለሚጋፉ እና ሉዓላዊነቷን የሚፈታተኑ አካላት ሲመጡ ግን በራችን በቅጡ መዘጋቱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት 100 ዓመታት ያጋጠሟትን የውጭ ጫናዎች እና ስትራቴጂክ ጥቅሟን የማደናቀፍ ሙከራዎችን በፅናት ማለፏን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁን ላይ ሀገሪቷ አቅሟን ወደ ላቀ ደረጃ እያሳደገች መሆኑን አመላክተዋል።
በተለይም የአየር ኃይልን የቴክኖሎጂ መራቀቅን አስመልክቶ ኢትዮጵያ Su-30 እና J-10 ያሉ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን የታጠቀች መሆኗን በመጥቀስ፤ አሁንም በድሮ ቴክኖሎጂ ላይ የሚገኙ ሀገራት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ቁመና መገንዘብ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
“ኢትዮጵያ ከምታውቋት ያለፈች ሀገር ናት” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከሀብቷ እና ከታሪኳም ባሻገር በፍጥነት እያደገች የምትገኝ ሀገር መሆኗን እና ይህንንም ዕድገት ምንም ዓይነት ፈተና እንደማያስቆመው አረጋግጠዋል።
“ለልጆቻችን የምናስረክባት ኢትዮጵያ ዜጎች በእኩልነት የሚስተናገዱባት፣ ጥቅማቸውን አሳልፈው የማይሰጡባት እና የከፋቸው በይቅርታ የሚታቀፉባት እውነተኛ እናት እንድትሆን በትጋት እየሠራን እንገኛለን” ብለዋል።
ከእንደዚህ ያለው ሀገር ጋር ተስማምቶ እና ተባብሮ አብሮ ማደግ ብቻ እንደሚያዋጣም አሳስበዋል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ
#EBC #EBCdotstream #Ethiopia #EthiopianAirForce90 #PMAbiy #blacklionairshow