Search

2 የጠላት ጀቶችን አየር ላይ ያጋጩት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ

እሑድ ጥር 17, 2018 942

ኢትዮጵያ በታሪክ ማኅደር ስማቸው በወርቅ ቀለም የተጻፉ የቁርጥ ቀን ልጆችን ያፈራች ኩሩ ሀገር ናት።

በተለይም የኢትዮጵያ አየር ኃይል አባላት አንጋፋ ካፒቴኖች፣ ቴክኒሻኖች፣ በምድር ላይ ሆነው ከሰማይ ንስሮቹ ጋር በቅንጅት የሚናበቡ ባለሙያዎች ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መከበርና ለድንበሯ መታፈር የማይተካ መስዋዕትነት ከፍለዋል።

በዚህ የጀግንነት ታሪክ ውስጥ እንደ ብርጋዴር ጄኔራል ለገሰ ተፈራ እና ካፒቴን በዛብህ ጴጥሮስ ያሉ ዕንቁ የሀገር ባለውለታዎች ጠላትን ዶጋ ዓመድ በማድረግ የኢትዮጵያን ክብር አስከብረው ታሪክ ሠርተዋል።

ይህ ትውልድ ተሻጋሪ የጀግንነት ዐሻራ፣ ዛሬም የአየር ኃይሉን ዓላማ ተረክበው ኢትዮጵያን ለሚጠብቁ አባላት ትልቅ የሞራል ስንቅና መነሳሻ መሆኑ አያጠያይቅም።

በዘመናዊ ትጥቅ፣ በላቀ ክህሎትና በሙሉ ዝግጁነት ራሱን ያደራጀው የኢትዮጵያ አየር ኃይል 90 ዓመት የምስረታ በዓሉን ሲያከብር የቀደመ ታሪኩን በክብር እያነሳ ለወደፊት ግቦቹ የሚረዳውን ዝግጁነትም ይበልጥ እያጠናከረ መሆኑን አስታውቋል።

 

በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ ስማቸው በጀግንነት ከሚነሱት አብራሪዎች መካከል ብርጋዴር ጄኔራል ለገሰ ተፈራ አንዱ ናቸው።

ኦስትሪያዊው የአቪዬሽን ዘርፍ ጋዜጠኛና የታሪክ አጥኚ ቶም ኩፐር ‘Wings over Ogaden’ በተሰኘው መጽሐፉ፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በኦጋዴን ጦርነት ያሳየውን ተጋድሎ "የአፍሪካ አየር ኃይል ታላቅ ድል" በማለት ይገልጸዋል።

ኩፐር በዚህ መጽሐፉ ብርጋዴር ጄኔራል ለገሰ ተፈራ በአየር ላይ የነበራቸውን ፍጹም የበላይነት በዝርዝር ያትታል።

በአዲስ አበባ የተወለዱት እና የሐረር ጦር አካዳሚና የበረራ ትምህርት ቤት ጥምር ምሩቅ የነበሩት ጀኔራል ለገሰ፣ የአየር ኃይሉ የጀርባ አጥንት ተደርገው የሚቆጠሩ ብርቅዬ አብራሪ ነበሩ።

በኋላም በአሪዞና በሚገኘው የአሜሪካ አየር ኃይል ኮሌጅ ተጨማሪ ስልጠና አግኝተዋል። 

1969 እስከ 1970 . በተካሄደው የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ወቅት፣ ብርጋዴር ጄኔራል ለገሰ ተፈራ ‘F5-E’ የተሰኘችውን የኢትዮጵያ የጦር ጄት በማብረር ባደረጉት የአየር ላይ ውጊያ በርካታ የሶማሊያ የጦር ጄቶችን መተው ከአየር ወደ መሬት በመጣል በካራማራ ደማቅ ታሪክ ጽፈዋል። 

በአየር ላይ ብቃታቸውም ጥቃት ለመፈፀም የመጡ 2 የዚያድ ባሬ ጦር ሚግ 21 ጄቶችን እርስ በርስ እንዲጋጩ በማድረግ እና ሌላ ጄት ላይ ጥቃት በማድረስ ታላቅ ጀብዱ ፈፅመዋል።

በወቅቱ የነበሩ የተለያዩ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አብራሪዎች የዚያድ ባሬን ወረራ ተከትሎ የመጡ 25 በላይ የተለያዩ ጄቶች እና አውሮፕላኖችን በማውደም እንዲሁም የጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ የእግረኛ ሠራዊት ዒላማዎችን ለይቶ በማጥቃት ሉዓላዊነትን መጠበቅ ማለት እስከምን ድረስ እንደሆነ አሳይተዋል።

በዚህ ሂደት የብርጋዴር ጄኔራል ለገሰ ተፈራ እና የሌሎችም የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች የአየር ላይ ብቃት አስደናቂ እንደነበር ታሪክ ሰንዶታል።

ኦስትሪያዊው ቶም ኩፐር እንደሚጠቅሰው፣ በጦርነቱ ወቅት የኢትዮጵያ የጦር ጄት አብራሪዎች በቁጥር ቢበለጡም፣ በላቀ የበረራ ክህሎት እና በጽኑ ጀግንነት ተለይተው በአየር ላይ ድልን በመቀዳጀት ፍጹም የበላይነት መውሰድ ችለዋል።

ብርጋዴር ጄኔራል ለገሰ ተፈራ በርካታ ጀብዱዎችን ከፈጸሙ በኋላ፣ በድሉ ዋዜማ በፊልቱ ግንባር የጦር ጄታቸው ስተመታ በፓራሹት ወርደው በጠላት እጅ ወደቁ። በዚህም 11 ዓመታት በሶማሊያ እስር ቤቶች ውስጥ እጅግ አሰቃቂ ሕይወትን አሳልፈዋል።

ሆኖም ግን ሁሉ ስቃይና መከራ ለሀገራቸው የነበራቸውን ፍቅርና ጽናት ሊያጠፋው አልቻለም። ከእስር ቆይታቸው በኋላም በክብር ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።

ለወደር የለሽ የጀግንነት ሥራቸውና ለከፈሉት ታላቅ መስዋዕትነት፣ በወቅቱ የሀገሪቱ ከፍተኛው የክብር ደረጃ የሆነው "የኅብረተሰብዓዊት ኢትዮጵያ ወደር የለሽ ጀግና ሜዳይ" ተሸልመዋል።

ብርጋዴር ጄኔራል ለገሰ ተፈራ ከካፒቴን በዛብህ ጴጥሮስና መሰል ጓዶቻቸው ጋር በአየር ላይ የፈጸሙት ተጋድሎ፣ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የተጣለ ጽኑ መሠረት ሆኖ ለዘላለም ሲዘከር ይኖራል።

በጌትነት ተስፋማርያም

#EBCDotstream #EBC #Ethiopia # EthiopianAirForce #anniversary #90years #ETAF90