Search

አለመግባባቶችን ለመፍታት ወሳኝ የሆነው የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት

ሰኞ ጥር 18, 2018 202

ውይይት አገናኝ ድልድይ፣ የሰከነ የጠረጴዛ ዙሪያ ንግግር ደግሞ የሰላምን ብርሃን የሚያሳይ የታሪክ ማጠፊያ ነውና፤ ኢትዮጵያ ዛሬ ይህንን የሰላም መንገድ የሙጥኝ ብላለች።
ኢትዮጵያ ለዘመናት የቆዩ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ልዩነቶቿን በዘላቂነት ለመፍታት የጀመረችው የሀገራዊ ምክክር ሒደት አሁን ላይ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡
በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አማካኝነት የሐሳብ የበላይነት የሚቀድምበትን ባህል በትውልድ ላይ ለመቅረፅ ትልቅ ጥረት እየተደረገ ነው።
የምክክር ኮሚሽኑ ሁሉን አቀፍ አጀንዳ በማሰባሰብ፣ ምቹ የምክክር መደላድሎችን በመፍጠር እና የጠረጴዛ ዙሪያ ንግግርን በማጎልበት ምክንያታዊ የውይይት ባህልን ለማዳበር የሚያስችሉ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል።
ምክክሩ ለኢትዮጵያውያን ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ለኢቢሲ ገልጸዋል።
 
የራስን ፍላጎት መግለፅ አግባብ ቢሆንም፣ የሌሎችንም መቀበል መቻል አስፈላጊ ነው ያሉት አቶ አደም ፋራህ፤ ምክክርን ማስቀደም እና ችግሮችን መፍታት ወሳኝ ተግባር ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የእኔ ሐሳብ ብቻ ልክ ነው፣ ፍጹምነት ከእኔ ጋር ነው ከሚለው እሳቤ በመውጣት ምክክርን መፍትሔ ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ጽንፈኝነትን ማዕከል አድርገው የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች በርካታ ችግሮችን ማስከተላቸውን ጠቁመው፤ ይህ ዓይነቱ አካሄድ የሚያበቃበትን መንገድ በማመቻቸት ምክክርን ማስቀደም እንደሚገባ ገልጸዋል።
ከጽንፈኝነት ይልቅ ሰላማዊ ውይይትን ይዞ መቅረብ እና በሐሳብ የበላይነት ማመን አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸዋል።
በሰከነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረጉ ውይይቶች መፍትሔዎችን በማመላከት የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት መደገፍ እንደሚገባም አመላክተዋል።
 
በአፎሚያ ክበበው