Search

“በሀገሩ ሉዓላዊነት የማይደራደር ሠራዊት ማፍራት ተጠናክሮ ይቀጥላል”- ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

ማክሰኞ ጥር 19, 2018 177

ወቅቱን የሚመጥን ሠራዊት የማፍራት ተልዕኮ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አየር ኃይል ላስመረቃቸው እጩ መኮንኖች ማዕረግ የማልበስ ሥነ-ሥርዓት አከናውነዋል።
በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግርም፣ “ኢትዮጵያ ቀደምት ሀገር በመሆኗ እና ካላት የጂኦ-ፓለቲካ አቀማመጥ አንጻር ጠላት ተደጋጋሚ ትንኮሳ ቢያደርግባትም ጀግኖች አርበኞች የተከበረች ሀገርን አስረክበውናል” ብለዋል።
በዘመናዊ ሠራዊት ግንባታ ደግሞ በሀገር ውስጥ እና በቀጠናው ሰላም በማስከበር እና ሽብርተኝነትን በመከላከል ረገድ ታሪክ የሠራ ሠራዊት ማፍራት መቻሉን ገልጸዋል።
በዓለም አቀፍ ምዘና መሠረትም የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ደረጃ መሻሻሉን የገለጹት ፊልድ ማርሻሉ፣ “የሀገራችን አቅም እንዲዳከም ጠላት ብዙ ቢሠራም ሠራዊታችን መክቶታል” ነው ያሉት።
በዚህም መንግሥት እና ሕዝብ ልማቱ ላይ ብቻ እንዲያተኩር አግዟል።
በሀገሩ ሉዓላዊነት የማይደራደር ሠራዊት ማፍራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያነሡት ፊልድ ማርሻሉ፣ አየር ኃይላችን የአየር ክልሉን ሳያስደፍር የቆየ ቢሆንም ባለፉት 30 ዓመታት ችግሮች የገጠሙት ቢሆንም በተደረገው ሪፎርም ሰፊ ለውጥ ማምጣት ተችሏል ብለዋል።
ተቋሙ ይህን ስኬቱን በ90ኛ ዓመት ክብረ በዓሉ ላይ ባሳየው ትርዒት መግለጥ መቻሉን አንሥተዋል።
ኢትዮጵያ በዘመናት መካከል በጀግኖች ልጆች መሥዋዕትነት የፀናች፣ ከሀገር ውስጥ አልፋ ለጎረቤት ሀገራት የሰላም ዋስትና መሆን የቻለች እንደሆነች ነው የገለጹት።
ከዚህም በላይ በአሁኑ ሰዓት በዓለማችን ጠንካራ ወታደራዊ ተቋም እየገነቡ ካሉ ሀገራት ተርታ አንዷ እየሆነች እንደምትገኝም ገልጸዋል።
በተመስገን እንዳለ