ዓለም አቀፍ ግንኙነት ንድፈ-ሐሳብ መነጽር ዓለም በሕግ ብቻ የምትመራ ሳይሆን የኃይል ሚዛን የሚገዛባት መድረክ ነች።
በዚህ መድረክ ላይ "ብሔራዊ ጥቅም" የሚባለው ቅዱስ ግብ ያለ ጠንካራ መከላከያ ኃይል ሊሳካ የማይችል ባዶ ምኞት ነው።
ስለዚህም ጠንካራ መከላከያ ኃይል የአንድ ሀገር የኢኮኖሚ፣ የዲፕሎማሲ እና የሥነ-ልቦና ጥንካሬ ማማ ነው።
ባለፉት 90 ዓመታት በከፍታ እና በዝቅታ ውስጥ የኢትዮጵያ የሉዓላዊነት እና የነፃነት ተምሳሌት ሆኖ የዘለቀው የኢትጵያ አየር ኃይልን ማጠናከር ያስፈለገውም ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞቿን የምታሳካበት ደጀን የሆነ ተቋም ለመፍጠር ታሳቢ ተደርጎ ነው።
ምክንያቱም አንዲት ሀገር ጠንካራ መከላከያ ሲኖራት፣ ተቀናቃኞቿ ጥቃት ከመሰንዘር ይልቅ ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲመጡ ትገፋፋለች። ይህንንም "ኃይልን ለሰላም መጠቀም" (Force for Peace) ይሉታል።
ታዋቂው ወታደራዊ ስትራቴጂስት ሰን ዡ (Sun Tzu) እንዳለው፣ "ታላቁ ድል ሳይዋጉ ማሸነፍ ነው"። ይህ ድል የሚገኘው ደግሞ ጠላት ሊያሸንፍ እንደማይችል በተረዳበት ቅጽበት ብቻ ነው።
ጠንካራ መከላከያ እና አየር ኃይል ሀገርን ከአውዳሚ ጦርነት በመታደግ የዜጎችን ሕይወት እና የሀገርን ሀብት ያተርፋል።
ስለሆነም አየር ኃይሉ ገናና ስም እና ዝና ቢኖረውም በተለይ ከደርግ መንግሥት ውድቀት ማግስት ለአንድ ሀገር አየር ኃይል አያስፈልግም ያለው ኢሕአዴግ ለተቋሙ ትኩረት በመንፈግ የቁልቁለቱን ጉዞ አሐዱ ብሎ ጀመረው።
ከአርባ ዓመታት በላይ ባገለገሉ እና ከጥቅም ውጪ በሆኑ አውሮፕላኖች የተሞላው ተቋም አይበለውና ሀገር ብትወረር እንኳ ፈጣን ምላሽ መስጠት በማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር።
በ2010 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው የለውጡ መንግሥት ኢትዮጵያን ሲረከብ፣ ለአየር ኃይሉ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት በሰው ኃይል፣ በትጥቅ እና በውጊያ መሠረተ ልማት የማጠናከር እንዲሁም ከባቢን የመቀየር ተግባር በስፋት መሥራቱ፣ አንድም የብሔራዊ ጥቅሜ ማረጋገጫ ስትራቴጂዬ ይሆናል ብሎ በማሰቡ ነበር።
ስለሆነም ባለፉት አምስት ዓመታት ተቋሙ የተጓዘባቸውን የ85 ዓመታት ሥራዎችን በፍጥነት በማከናወን እጅግ ከዘመነው ዓለም ጋር ተወዳዳሪ አየር ኃይል ለመፍጠር በቀጥተኛው መንገድ በመጓዝ ውጤት ማምጣት መጀመሩ አንድምታው ትልቅ ሆኗል።
ዲፕሎማሲ "የቃላት ጨዋታ" ብቻ አይደለም፤ ከቃላቱ ጀርባ ያለውን አቅም የሚለካ ጥበብ እንጂ። ጠንካራ መከላከያ የሌለው ዲፕሎማት በድርድር ወቅት ጥርስ እንደሌለው አንበሳ ነው።
በአንጻሩ፣ ጠንካራ ጦር ያላት ሀገር በክልላዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ አጀንዳ ቀራጭ እንጂ ተከታይ አትሆንም።
ብሔራዊ ጥቅሟን የሚነኩ ስምምነቶች እንዳይፈረሙ የማስቆም ወይም እንዲሻሻሉ የማድረግ "የመደራደር ጡንቻ" የምታገኘው ከሠራዊቷ ጥንካሬ ነው።
በሌላ በኩል ጠንካራ ጦር ያላቸው ሀገራት በንግድ፣ በድንበር ጉዳዮች እና በቀጠናዊ ተፅዕኖ ዙሪያ በሚደረጉ ድርድሮች ላይ ቃላቸው ክብደት እንዲኖረው እና ጥቅማቸው እንዲከበር ያደርጋሉ።
በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የሚደረጉ ድርድሮች ውጤታማ የሚሆኑት ሀገሪቱ ጥቅሟ ሲነካ የምትወስደው እርምጃ ግምት ውስጥ ሲገባ ነው።
ስለዚህም ኢትዮጵያ አየር ኃይልን መሰል የፀጥታ ተቋሞቿ ላይ ትኩረት ሰጥታለች፤ እንደውም አንዳንዶች "መከላከያ ሠራዊት ወይም አየር ኃይል ለምን ከፍተኛ ትኩረት በመንግሥት ይሰጣቸዋል?” ብለው ይጠይቃሉ።
መልሱ ቀላል ነው፦ ሰላም ከሌለ ኢኮኖሚ ስለሌለ፤ ሰላም ከሌለ የዜጎች ሕይወት አደጋ ላይ ስለሚወድቅ ነው።
ለአብነት ያህል እንደ ግድቦች፣ የኃይል ማመንጫዎች እና የትራንስፖርት መስመሮች ያሉ የብሔራዊ ጥቅም ማሳያዎች በዘመናዊ አየር ኃይል እና መከላከያ ሠራዊት ካልተጠበቁ ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው።
“የውጭ ኢንቨስተሮች ካፒታላቸውን የሚያፈስሱት ዋስትና ባለው እና ጠንካራ የደኅንነት መዋቅር ባረጋገጠ ሀገር ውስጥ ነው” የሚለውም ምላሽ ይሆናል።
አሁን ላይ የኢፌዴሪ አየር ኃይል ከአንድ ወገን ወይም ቡድን ይልቅ ለሀገራዊ ዓላማ የቆመ ተቋም ሆኗል። የብሔራዊ አንድነት ምልክትም ነው።
ዜጎች በሀገራቸው መከላከያ ሲተማመኑ፣ በሥነ-ልቦና የታነፀ እና ለልማት የተነሣሣ ማኅበረሰብ ይፈጠራል። ይህ የሕዝብ ወገንተኝነት እና ሞራል ደግሞ ለማንኛውም የውጭ ወረራ የማይበገር "የማይታይ ግንብ" ይፈጥራል።
በአጭሩ የ90 ዓመታት የውጣ ውረድ መንገድን የተጓዘው አየር ኃይሉ፣ መጠነ ሰፊ የግንባታ ሥራዎች እየተከናወኑለት መሆኑ ለጦርነት መዘጋጀት ሳይሆን፣ ብሔራዊ ጥቅምን ያለ ስጋት ለማስከበር የሚከፈል ዋጋ ነው።
ሀገራት በዓለም መድረክ ያላቸው ክብር የሚመነጨው ከቤታቸው ጥንካሬ ነው። በመሆኑም፣ አየር ኃይልን ማዘመን እና ማጠናከር ለነገ የማይባል የህልውና እና የብሔራዊ ጥቅም ማረጋገጫ ዋስትና ነው።
ጠንካራ አየር ኃይል የአንድ ሀገር የሉዓላዊነት ምልክት ብቻ ሳይሆን፣ ብሔራዊ ጥቅምን ለማረጋገጥ የሚያገለግል ዘርፈ ብዙ መሣሪያ ነው።
አየር ኃይሉ በዘመናዊ ትጥቅ፣ በቴክኖሎጂና በሥነ-ልቦና ሲገነባ፣ ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላት ክብርና ጥቅሟን የማስከበር አቅሟ እኩል ከፍ ይላል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተሰሚነት እና የዲፕሎማሲ ተፅዕኖ (Soft Power) ለማሳደግ አየር ኃይሉ ትልቅ ድርሻ አለው።
የጎረቤት ሀገራት ሰላም ሲታወክ ፈጣን የሎጂስቲክስ እና የወታደራዊ ድጋፍ በመስጠት ቀጠናዊ መረጋጋትን ያረጋግጣል፤ ይህም ለኢትዮጵያ ሰላም ዋስትና ነው።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል "የአየር ክልላችን ጠባቂ" ብቻ ሳይሆን፣ የሀገሪቱ የልማት፣ የቴክኖሎጂ እና የዲፕሎማሲ አቅም መገለጫ ነው። አቅሙ በጠነከረ ቁጥር የኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ የመደራደር እና ጥቅሟን የማስከበር አቅሟ አብሮ ያድጋል።
ስለሆነም የመደመር መንግሥት የተቋማት ግንባታ ለሀገረ መንግሥት መፅናት መሠረት ነው ብሎ አየር ኃይሉን በቴክኖሎጂ እና በሰው ኃይል ማዘመን፣ ማደራጀት መጀመሩ በእርግጥም ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ ኩራት ሊሆን የሚችል ተግባር ነው።
በቶማስ ኃይሉ
#EBC #Ebcdotstream #Ethiopia #Airforce #ethiopianairforce90