Search

ሰላምን በዝግጅት፣ ሉዓላዊነትን በጥንካሬ - የኢትዮጵያ ጉዞ

ሓሙስ ጥር 21, 2018 317

ኢትዮጵያ "ሰላምን ከፈለግህ ለጦርነት ተዘጋጅ" የሚለውን ጥንታዊ የጦር ሳይንስ መርህ የህልውናዋ መሠረት በማድረግ፣ ጦርነትን አስቀድሞ የመከላከል (Deterrence) ጥበብን የተላበሰ ዘመናዊ የመከላከያ ግንባታ እያከናወነች ትገኛለች።
ይህ ዝግጅት ጦርነትን የመናፈቅ ሳይሆን፣ ጥቃትን በዝግጁነት የመግታት ስትራቴጂያዊ ግብ ያለው ነው። ከታሪክ ሂደት መገንዘብ እንደሚቻለው ድካም ጠላትን ይጋብዛል፤ ዝግጁነት ግን ጥቃትን ያመክናል።
ኢትዮጵያ በታሪኳ የሌላን ሀገር ድንበር ገፍታ በሌሎች ሉዓላዊነት ጣልቃ ገብታ አታውቅም፤ ነገር ግን ሰላሟን የሚነሱ ኃይሎች ሲነሱም አሳፍራ ከመመለስ ቦዝና አታውቅም።
ዛሬ እያከናወነችው ያለው ዘመናዊ የመከላከያ ግንባታ፤ ጥንታዊውን የሀገር መከላከያ ጽናት ከዘመኑ የቴክኖሎጂ ልዕልና ጋር የማቀናጀት ስትራቴጂያዊ ጉዞ ነው።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እያከናወነ ያለው ትልቅ ሪፎርም በሦስት ዋና ዋና ስትራቴጂያዊ ምሰሶዎች ላይ የተመሰረተ ነው።
የመጀመሪያውና ቀዳሚው የአየር ኃይል የበላይነት ነው። ሰማይዋን የማይደፈር ለማድረግ የታጠቀቻቸው ዘመናዊ ተዋጊ ጄቶች እና የሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች)፣ የጠላትን የጥቃት ፍላጎት ገና ከሩቁ መግታት የሚያስችል አቅም ፈጥረዋል።
ይህ አቅም ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ድልን ከመቀዳጀት ባለፈ፣ ጠላቶች በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ከመሰንዘራቸው በፊት ደጋግመው እንዲያስቡ የሚያደርግ የኃይል ተጽዕኖ ፈጥሯል። የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዛሬ የሀገር አለኝታ ብቻ ሳይሆን የቀጠናው የሰላም ሚዛን ጠባቂ ሆኗል።
ሁለተኛው እና የሠራዊቱ መዘመን መገለጫ የዲጂታል እና የሳይበር ደኅንነት ግንባታ ነው። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ጦርነት በሳይበር ዓለምም የሚካሄድ መሆኑን ከግምት በማስገባት፣ በመከላከያ መዋቅር ውስጥ በሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤ አይ) የታገዘ የመረጃ ሥርዓት ተገንብቷል።
ይህ በቴክኖሎጂ የዳበረ ሠራዊት፣ ድንገተኛ ጥቃቶችን አስቀድሞ ለመለየት እና ሀገራዊ መሠረተ ልማቶችን ከማንኛውም የጠላት ትንኮሳ በንቃት ለመጠበቅ በተጠንቀቅ ላይ ይገኛል።
ሦስተኛው ለሁሉም መሠረት የሆነው ብቁና ፕሮፌሽናል የሆነ የሰው ኃይል ግንባታ ነው። ክኖሎጂውን የሚመራው የሰው አዕምሮ በመሆኑ፣ ቀድሞ ተቋርጠው የነበሩ የጦር አካዳሚዎች በዘመናዊ መልኩ ተደራጅተው ሥራ ጀምረዋል።
እነዚህ ተቋማት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ፣ በወታደራዊ ሳይንስ የሰለጠኑ እና በጠንካራ የሀገር ፍቅር የታነጹ መኮንኖችን እያፈሩ ይገኛሉ።
ይህ አጠቃላይ ዝግጅት ኢትዮጵያ የምትፈልገውን ሰላም በጥንካሬ እንድታረጋግጥ ያስችላታል። ሰላሟ የሚጸናው በዝግጅቷ ልክ በመሆኑ፣ ጠንካራ መከላከያ መገንባት ለኢትዮጵያ አማራጭ የሌለው የሰላም መንገድ ነው።
በለሚ ታደሰ