ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአይሻ-2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ምረቃ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ የሚጠበቀው የአፍሪካ የብልጽግና ዘመን ቀዳሚ ምሳሌ ለመሆን በቁርጠኝነት እየሠራች መሆኑን ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያዎቹ 25 ዓመታት የምዕራባውያን፣ ሁለተኛው ሩብ ደግሞ የእስያ ሀገራት የዕድገት ማማ ላይ የሚደርሱበት መሆኑን ገልጸው፤ ሦስተኛው እና አራተኛው ሩብ ክፍለ ዘመን ግን የአፍሪካ ዘመን የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል።
ይህን ዕድል ለመጠቀምም ኢትዮጵያ በሕፃናት ትምህርት እና በመሠረተ ልማት (መንገድ፣ ቴሌኮም እና መብራት) ላይ ትኩረት አድርጋ እየሠራች መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የምታስመዘግበው ዕድገት ተፈጥሮን የማይጎዳ መሆን እንዳለበት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ እንዲሁም የንፋስ እና የጂኦተርማል ኃይል ልማቶች የሀገሪቱን የንጹህ ኢነርጂ ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ ለአፍሪካ አርአያ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ዛሬ የተመረቀው የአይሻ-2 የንፋስ ኃይል ማመንጫም የዚሁ አካል መሆኑን አክለዋል።
"የኢትዮጵያ ዕድገት ከጎረቤት ሀገራት ትሥሥር ውጭ ብቻውን ሊረጋገጥ አይችልም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ከጅቡቲ ጋር ያለው ጠንካራ የባቡር፣ የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ እና የውኃ ትሥሥር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ከሱዳን፣ ከኬንያ እና ከታንዛኒያ ጋር በተመሳሳይ እነዚህን ነገሮች የምንጋራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከሶማሊያ እና ከደቡብ ሱዳን ጋር በመንገድ እና በመብራት ለመተሣሠር ጥረት መጀመሩን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ በዓመቱ ልታሳካ ከያዘችው ዕቅድ ባለፉት 6 ወራት ብቻ 78 በመቶ የሚሆነውን ማሳካት መቻሏን ጠቅሰው፣ ሀገራችን በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በታዳሽ ኢነርጂ እና በከተሞች ውበት ላይ ባከናወነቻቸው ሥራዎች ምክንያት COP32 ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባዔ በኢትዮጵያ እንዲካሄድ መወሰኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል። ይህም ለሀገሪቱ ትልቅ እውቅና መሆኑን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአይሻ-2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናው ሀገራት ጭምር የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መሆኑን ተናግረዋል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ
#ebcdotstream #AbiyAhmed #Ethiopia #አይሻ2 #development