Search

ከውሃው በታች የታሪክ ምስጢር የያዘው የሪፍት ቫሊው ዕንቁ

እሑድ ጥር 24, 2018 111

ስለ ደንበል ሐይቅ ውበት ሲነገር ሰምተው ይሆናል፤ ስለ ደሴቶቹ ምስጢርና ስለ ጥንታውያኑ ገዳማትስ ምን ያውቃሉ? የታቦተ ጽዮን ማረፊያ እንደነበረች ከሚነገርላት ደሴት ጀምሮ፣ በሐይቁ ላይ የሚታዩት ድንቅ ተፈጥሮዎች ለምን 'የሪፍት ቫሊው ዕንቁ' እንደሚያሰኙት አብረን እንቃኝ።
በኦሮሚያ ክልል በባቱ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘው የደንበል ሐይቅ 440 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ስፋት ያለው ሲሆን፣ በአማካይ ደግሞ 4 ሜትር ያህል ጥልቀት ያለው ሐይቅ ነው፡፡
የሐይቁ መለያ የሆኑ 5 ደሴቶችን የያዘ ሲሆን እነሱም፦ ቱሉ ጉዶ፣ ገሊላ፣ ደብረ ሲና፣ ጣደቻ እና ገነተ ማርያም በመባል ይታወቃሉ።
በተለይም በ10ኛው ክፍለ ዘመን የአክሱም ጽዮን ታቦት ለ70 ዓመታት ያህል በቱሉ ጉዶ ደሴት በሚገኘው የማርያም ጽዮን ገዳም ተጠብቆ መቆየቱ ሐይቁን ለሃይማኖታዊ ቱሪዝም ተመራጭ እና 'የሪፍት ቫሊው ዕንቁ እንዲባል ምክንያት ሆኗል።
ዛሬም ድረስ በእነዚህ ገዳማት ውስጥ ጥንታዊ የብራና መጻሕፍት እና ሌሎች ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ ቅርሶች ይገኛሉ።
በኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ ከሚገኙት ተፈጥሮአዊ ሐይቆች መካከል በታሪካዊ ስፍራነቱና በብዝሃ-ሕይወት ሀብቱ ቀዳሚ ስፍራ የሚይዘው የደንበል (ባቱ) ሐይቅ፣ የአካባቢው የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ሆኖም እያገለገለ ይገኛል።
ሐይቁ ከውበቱ ባሻገር ለሀገሪቱ ታሪክ ትልቅ ምስጢር አዝሎ የቆየ የጥበብ መገኛ ተደርጎ ይወሰዳል።
ከ60 በላይ የውኃ ላይ አዕዋፋት ዝርያዎች መገኛ የሆነው የደንበል ሐይቅ በተለይ ፔሊካኖች፣ ፍላሚንጎዎችና ነጭ ክሬኖች የተጓዥ ቱሪስቶች ዐይን ማረፊያዎች ናቸው።
በአካባቢው በስፋት የሚገኘው የዓሳ ምርትም ለማህበረሰቡ ዋና የኢኮኖሚ ምንጭ በመሆንም እያገለገለ ይገኛል።
እናንተስ ይህን ድንቅ እና ልዩ ስፍራ ጎብኝታችሁ ታውቃላችሁ? በአስተያየት መስጫው ሃሳባችሁን አጋሩን፦
በሜሮን ንብረት