Search

የቤት ባለቤትነት ህልምን እውን ለማድረግ በኦሮሚያ ክልል በ6 ወራት ውስጥ ብቻ ከ116 ሺህ በላይ ቤቶች ተገንብተዋል

እሑድ ጥር 24, 2018 130

በኦሮሚያ ክልል እየጨመረ የመጣውን የቤት ፍላጎትና አቅርቦት ለማጣጣም በተከናወኑ የተቀናጁ ጥረቶች፣ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 116 ሺህ 429 ቤቶች ተገንብተው መጠናቀቃቸውን የክልሉ ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ አስታውቋል።
 
ይህ ታላቅ ስኬት የተመዘገበው በዘርፉ የተሰማሩ ማኅበራትን በማደራጀትና የባለሀብቶችን አቅም በስፋት ጥቅም ላይ በማዋል ሲሆን፣ በዚህም በማኅበር ተደራጅተው ሲጠባበቁ ከነበሩ ዜጎች መካከል 16 ሺህ 127 አባላት የራሳቸው መኖሪያ ቤት ባለቤት መሆን ችለዋል።
 
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ብርሃኑ በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ክልሉ ከአዳዲስ ግንባታዎች ባሻገር ለአቅመ ደካማ ወገኖችም ልዩ ትኩረት በመስጠት በዜግነት አገልግሎት በርካታ ቤቶችን የማደስ ተግባር በስፋት እያከናወነ ይገኛል።
 
በተጨማሪም የአከራይና ተከራይ አዋጅን ውጤታማ በሆነ መንገድ ተግባራዊ በማድረግ፣ በተከራዮች ላይ ይደርስ የነበረውን ኢኮኖሚያዊ ጫና በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ መቻሉ የዘርፉ ሌላኛው ስኬት ሆኖ ተመዝግቧል።
 
ቢሮው ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹና ዘመናዊ ለማድረግ በሚያደርገው ጉዞ፣ ሕገ-ወጥ የቤት ግንባታንና አያያዝን ለመከላከል ጥብቅ ቁጥጥር እያደረገ ሲሆን፣ በቀጣይም የከተማ ነዋሪዎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማትና የአገልግሎት ማዘመን ሥራዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

 

በለሚ ታደሰ