ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል የዓለም የዕድገት መዋቅር እና ተቋማት ለምዕራባውያን አገራት መልሶ ግንባታ ብቻ ትኩረት በመስጠታቸው፣ ቀሪው ዓለም በተለይም አፍሪካ በጨለማ ውስጥ እንድትቆይ መደረጉ ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአይሻ-2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ምረቃ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ “21ኛው ክፍለ ዘመን ይህንን የታሪክ ሂደት የሚቀይር አዲስ እይታ እና የዕድገት አቅጣጫ ይዞ ብቅ ብሏል” ብለዋል።
የታሪክና የኢኮኖሚ ምሁራን እንደሚጠቁሙት፣ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያዎቹ 25 ዓመታት የምዕራቡ ዓለም ዕድገት ከፍተኛው ደረጃ ላይ የደረሰበት ወቅት ነበር።
በቀጣዮቹ 25 ዓመታት ደግሞ የዓለም የኢኮኖሚ ማማ ወደ ኤዥያ ሀገራት እንደሚዞር ምልክቶች የታዩ ሲሆን፣ የክፍለ ዘመኑ ሁለተኛ አጋማሽ ግን ፍጹም "የአፍሪካ ዘመን" የመሆን ዕድሉ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።
ለምን አፍሪካ? ለዚህ ታሪካዊ ሽግግር ዋነኛው ምክንያት ከአህጉሪቱ የሰው ኃይል አቅም ጋር የተያያዘ ነው የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከ25 ዓመታት በኋላ በዓለም ላይ ካሉ አራት ሰዎች መካከል አንዱ አፍሪካዊ እንደሚሆን ይገመታል ብለዋል።
ይህ ግዙፍ ቁጥር ብቻ ሳይሆን፣ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ያለው ወጣት ትውልድ የዛሬውን የቴክኖሎጂ ዓለም በትክክል አንብቦ የመጠቀም አቅም ያለው በመሆኑ፣ አዳዲስ ነገሮችን ለመፍጠር፣ ለመስራት እና ኢኮኖሚውን ለማስፋት ትልቁ የሰው ኃይል የሚገኘው በአፍሪካ ምድር ላይ መሆኑን አመላክተዋል።
አህጉሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት የፈጠራ ክህሎት ካለው ወጣት ኃይል ጋር ማቀናጀት ከተቻለ፣ 21ኛው ክፍለ ዘመን አፍሪካ ከዳር ተመልካችነት ወጥታ የዓለም የኢኮኖሚና የሥልጣኔ ማዕከል የምትሆንበት ወርቃማ ዘመን እንደሚሆን ይጠበቃል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።