የነገውን ብርቱ ውድድር ለማሸነፍ የዛሬው ዝግጅት ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ወጣቶችን ለላቀ ስኬት ለማብቃት መንግሥት በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከሀገሪቱ አምስት የዕድገት ምሰሶዎች መካከል አንዱ ቴክኖሎጂ እንዲሆን መደረጉ ለትውልድ የተሰራ ትልቅ ኢንቨስትመንት መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተለይም በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ረገድ ኢትዮጵያ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እየከፈተች መሆኗን አብራርተዋል።
በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ በዓለም ሁለተኛ የሆነውን ግዙፍ የኤአይ (AI) ዩኒቨርሲቲ ለመገንባት በከፍተኛ ፍጥነት እየሰራች ሲሆን፣ ይህ ታላቅ የትምህርት ተቋም በሚቀጥለው አንድ ዓመት ውስጥ ሥራ እንደሚጀምር ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም አባቶቻችን የኢትዮጵያ አየር መንገድን ገንብተው በዓለም ስመጥር እንዳደረጉት ሁሉ፣ ይህ ዩኒቨርሲቲም ለኢትዮጵያ ልጆች የተሻለ ዘመንን እና ብሩህ የወደፊት እድልን ይዞ እንደሚመጣ ተናግረዋል።
ይህ በቴክኖሎጂ የታገዘ የትውልድ ዝግጅት ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረክ ተወዳዳሪ ከማድረጉም ባለፈ፣ ለልጆቻችን የምናወርሰው ታላቅ የጥበብ እና የእውቀት መሠረት እንደሚሆን ይጠበቃል ብለዋል።