Search

ወጣቱን ለነገው ዓለም ማዘጋጀት፡ የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂና የሰው ኃይል ግንባታ ራዕይ

ማክሰኞ ጥር 26, 2018 227

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለምክር ቤት አባላት በሰጡት ምላሽ ወጣቶችን ስለማብቃት ማብራሪያ ሰጥተዋል። መንግሥት ቀጣዩን ትውልድ ለወደፊት የሥራ ዓለም ለማዘጋጀት በትኩረት እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ ከ25 ዓመታት በኋላ ከዓለም ሕዝብ አንድ አራተኛው አፍሪካዊ ይሆናል። በዚያን ወቅት ለሥራ የሚፈለገው ወጣት ኃይል በብዛት የሚገኘው በአፍሪካ ነው። የአህጉሪቱ የሕዝብ ቁጥር በሥርዓት ከተመራ ለኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ ዕድል መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ውስጥ አፍሪካ 450 ሚሊዮን አዳዲስ ወጣቶችን ለሥራ ታዘጋጃለች። ይህም በአህጉሪቱ ለሥራ ዝግጁ የሆሚሆነውን የሰው ኃይል 1.1 ቢሊዮን ያደርሰዋል። ይህ ቁጥር በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚፈለገውን የሰው ኃይል 50 በመቶ የሚሸፍን ይሆናል።

ኢትዮጵያ ይህንን ታሪካዊ ዕድል ለመጠቀም ወጣቶቿን በቴክኖሎጂ እያነጸች ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። በተለይም በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩትን ስታቋቁም በአፍሪካ ቀዳሚ ከሆኑት ሀገራት አንዷ እንደሆነችም ተናግረዋል።

በቅርቡ የሚመረቀው የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ በዓለም ላይ ሁለተኛው መሆኑም ተገልጿል። ይህ ትልቅ ተቋም የወደፊቱን ትውልድ ታሳቢ አድርጎ የተገነባ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡፡

እስካሁንም አበረታች ውጤቶች የተገኙ መሆኑን ጠቅሰው፣ በቀጣይ ዓመታት ዘመን ተሻጋሪ ስኬቶች እንደሚመዘገቡ አረጋግጠዋል።