Search

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ጉዞ እና የነገው ትውልድ ስንቅ፦ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ማብራሪያ የተወሰዱ ዋና ዋና ነጥቦች

ማክሰኞ ጥር 26, 2018 125

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ከማብራሪያቸው የተወሰዱ ቁልፍ ነጥቦች እነሆ፦
👉🏽የኢኮኖሚ ሪፎርም እና ውጤቱ፦ ባለፉት ዓመታት የተካሄደው የኢኮኖሚ ሪፎርም ዋነኛ ግብ የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራትን መፈወስ ነው። ግብርና ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ የነበረውን መዋቅር በመቀየር፣ ብዝኃ-ዘርፍ ኢኮኖሚን በመከተል ጥራት ያለው ዕድገት ማስመዝገብ ተችሏል።
ይህም በኢትዮጵያ ታሪክ አመርቂ ውጤት የታየበትና ማንንም የማያከራክር ዕድገት የመጣበት ወቅት ሆኗል።
👉🏽የብድር ጫና እና ፋይናንስ፦ ኢትዮጵያ ላለፉት 20 ዓመታት በነበረው ጤናማ ያልሆነ አበዳደር ምክንያት ብድር መበደር የማትችልበት ደረጃ ላይ ደርሳ ነበር። አሁን ግን ይህንን ጫና በመቅረፍ የሀገሪቱን የፋይናንስ ቁመና ለማስተካከል ከፍተኛ ሥራ ተሰርቷል።
👉🏽አፍሪካ እና የነገው ውድድር፦ በአውሮፓውያኑ 2050 የዓለም ሕዝብ 9.8 ቢሊየን ሲደርስ፣ 2.5 ቢሊየኑ አፍሪካዊ ይሆናል። ከ10 ዓመት በኋላ ዓለም ለሥራ ከሚፈልጋቸው ሰዎች መካከል ግማሹ አፍሪካ ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ፣ ወጣቶቻችንን ለዚህ ዓለም አቀፍ ውድድር ማዘጋጀት የዛሬ የቤት ሥራችን ነው።
👉🏽የትውልድ አደራ፦ "የዛሬው ድህነት እኛ ላይ አብቅቶ ወደ ልጆቻችን እንዳይሸጋገር መሥራት አለብን" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሕዝብ ቁጥርን በሥርዓት በመምራት ለኢኮኖሚ ዕድገት እንዲውል ማድረግና ትውልድ ላይ ኢንቨስት ማድረግ የመንግሥታቸው ቀዳሚ ትኩረት መሆኑን አረጋግጠዋል።