የ2026 አዲስ ዓመት በባተ በመጀመሪያዎቹ 36 ቀናት ውስጥ ብቻ አዲስ አበባ የዓለማችን ታላላቅ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ መናኸሪያ መሆኗን ዳግም አስመስክራለች።
ይህ የዲፕሎማቶች መመላለስ በአጋጣሚ የመጣ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ የጂኦ-ፖለቲካ ሽኩቻዎችን በብልሃት በማለፍ የሆነ ሚዛናዊና በብሔራዊ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ እየተገበረች መሆኑን ማሳያ ነው።
ከአውሮፓ እስከ እስያ፣ ከአሜሪካ እስከ መካከለኛው ምስራቅ ያሉ የኃያላን ሀገራት ተወካዮች ተከታታይ ጉብኝት፤ የኢትዮጵያን ቀጣናዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነትና የተሳካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።
በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ የአሜሪካ፣ የቻይና፣ የጀርመን፣ የዩናይትድ ኪንግደም፣ የኖርዌይ፣ የጃፓን፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች እና የኦማን ከፍተኛ ዲፕሎማቶች በአዲስ አበባ መገኘታቸው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ስትራቴጂካዊ ሚዛን ዳግም አረጋግጧል።
በተለይም የአሜሪካ እና የቻይና ተወካዮች በተመሳሳይ ወር አዲስ አበባ መገኘታቸው ኢትዮጵያ በኃያላኑ መካከል ያለውን የጂኦ-ፖለቲካዊ ሽኩቻ ወደ ጎን በመተው፣ ለሁሉም ወዳጅ የሆነና በብሔራዊ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ሚዛናዊ ፖሊሲ እየተከተለች መሆኑን ያሳያል።
ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ላይ በግልጽ እንዳስቀመጠችው፣ ከየትኛውም ሀገር ጋር ለሚኖራት ግንኙነት ቅድሚያ የምትሰጠው ለሀገራዊ ጥቅም ነው። ይህም ግንኙነቷን ከእርዳታ ጥገኝነት ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ትብብር እያሸጋገረው ይገኛል።
ይህ ስኬት ኢትዮጵያ በብሪክስ አባልነቷ ከምሥራቁ ዓለም ጋር ያላትን ጥብቅ ትብብር እያጠናከረች፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከምዕራባውያኑ ጋር ያለባትን የንግድ እና የደህንነት አጋርነት በተመሳሳይ ፍጥነት እያስቀጠለች መሆኑን ያረጋገጠ ነው።
ግንኙነቷን ከእርዳታ ጥገኝነት ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ትብብር እያሸጋገረች መሆኗን ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር የተደረገው የአረንጓዴ ኢነርጂ ስምምነት እና ከሌሎች ሀገራት ጋር የታለሙ የኢንቨስትመንት አቅጣጫዎች ምስክር ናቸው።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር እና በመካከለኛው ምስራቅ ባለው ቁርኝት ላይ ጉልህ ስኬቶችን እያስመዘገበች ይገኛል።
ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጋር ያለው ጥብቅ ግንኙነት እና ከአሜሪካ የአፍሪካ ወታደራዊ ኃይል (AFRICOM) ጋር የተደረገው ውይይት ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ፀረ-ሽብር ትግል እና ቀጠናዊ መረጋጋት ውስጥ ያላትን የማይተካ ሚና ዳግም አፅንኦት ሰጥቶታል።
በአጠቃላይ አዲስ አበባ የዲፕሎማሲው ጨዋታ መለወጫ (Game Changer) መሆኗን በ2026 መጀመሪያ በተግባር አሳይታለች። እነዚህ ዲፕሎማሲያዊ ድሎች ወደ ተጨባጭ ኢንቨስትመንት እና ዘላቂ የኢኮኖሚ ጥቅም በመቀየር ላይ መሆናቸው ለኢትዮጵያ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፋች ሆኗል።
በለሚ ታደሰ
#EthiopianBroadcastingCorporation #Diplomacy #center #Ethiopia
ተጨማሪ የኢቢሲ ዶትስትሪም የዲጂታል አማራጭ አድራሻዎችን ከአስተያየት መስጫ ሳጥን ያግኙ፡-