በአዲስ አበባ ስታዲየም የተካሄደው 1447ኛው የዒድ አል-ፈጥር የሶላት ሥነ-ሥርዓት፣ የሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ በስኬት መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፣ የእምነቱ አባቶች፣ የውጭ ሀገር አምባሳደሮችና በርካታ ምእመናን ተገኝተዋል።
የሶላት መርሐ-ግብሩ በስኬት እንዲጠናቀቅ የጸጥታ አካላት አስቀድመው ባወጡት ዕቅድ መሠረት፣ ከኢትዮጵያና ከአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤቶች ጋር በጋራ በመሥራታቸው ስኬታማ ተግባር ማከናወን ተችሏል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የሶላት ሥነ-ሥርዓቱ በስኬት እንዲከበር የበዓሉ ታዳሚዎች ከጸጥታ አካላት ጎን በመቆም ላደረጉት ተገቢ ትብብር ምስጋናውን አቅርቧል።
ለመላው የእምነቱ ተከታዮች በዓሉ የሰላምና የደስታ እንዲሆን መልካም ምኞቱን የገለጸው መምሪያው፣ የከተማዋን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር በሚከናወኑ ተግባራት ላይ ኅብረተሰቡ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።