በአሰብ ከተማ ነግደው ያተረፉ፣ ወልደው የከበሩና ከተማዋን ያቀኑ ኢትዮጵያውያን፤ ዛሬ በኮምቦልቻ ከተማ "የአሰብ ተፈናቃዮች" በሚል መጠሪያ በራሳቸው መንደር ማህበር መስርተው ይኖራሉ።
ኢቢሲ የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በእነዚህ ነዋሪዎች ዘንድ ተገኝቶ ባደረገው ቆይታ፣ ነዋሪዎቹ ሀብትና ንብረታቸውን በአሰብ ጥለው ቢመጡም አሁንም ድረስ ስለ ከተማዋ ጥልቅ ትዝታና ቁጭት እንዳላቸው ታዝቧል።
የኮምቦልቻ ከተማ የመንግስት ኮሚኒኬሽን መመሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ዘሪቱ ሁሴን እንደገለጹት፤ እነዚህ ወገኖች ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በከተማዋ በቋሚነት እየኖሩ ይገኛሉ።
ቀደም ሲል በአሰብ በንግድ ስራ ይተዳደሩ የነበሩት አቶ አሊ ኢድሪስ፣ አሰብ የሁሉም አካባቢ ህዝብ የሚገናኝባት "የፍቅር ከተማ" እንደነበረች ያስታውሳሉ።
አቶ አሊ አክለውም ቀይ ባህር ለኢትዮጵያ እንደ ልብና አእምሮ ትልቅ ዋጋ ያለው መሆኑን ገልጸው፣ ኢትዮጵያ ዳግም የባህር በር ባለቤት ብትሆን የብልጽግና ማማ ላይ ለመድረስ እንደሚያስችላት በልበ ሙሉነት ይናገራሉ።
በወቅቱ በባህር ትራንስፖርት ዘርፍ ያገለግሉ የነበሩት አቶ ሲሳይ አሰፋ፣ የባህር በሩ ለኢትዮጵያ እንደ እናትና እንደ ብርሃን እንደነበር በቁጭት ያወሳሉ።
ኢትዮጵያ የባህር በር በመነጠቋ ምክንያት እንደ ሌሎች የሰለጠኑ ሀገራት እንዳታድግ እንቅፋት እንደሆነባትም ይገልጻሉ።
ሌላው ነዋሪ አቶ ከበደ ኃይሉ በበኩላቸው፣ አሰብ ቀደም ሲል የወሎ ክፍለ ግዛት አካል እንደነበር አስታውሰው፣ በወቅቱ የነበሩ ግዙፍ መሰረተ ልማቶችን ጥለው ለመውጣት መገደዳቸውን ይገልጻሉ።
የአሰብ ተፈናቃዮች በኮምቦልቻ የራሳቸውን መንደር መስርተው ከመኖራቸው ባሻገር፣ በመካከላቸው ባለው ጠንካራ ትስስር ትዝታቸውን ይጋራሉ፤ እርስ በእርሳቸውም ይረዳዳሉ።
ነዋሪዎቹ ኢትዮጵያ የባህር በሯን ያጣችው በታሪካዊ ስህተት መሆኑን በመጥቀስ፣ አሁን መንግስት የጀመረውን ጥረት ህዝቡ ሊደግፈው እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
እድሜ ሰጥቷቸው ያ ታሪካዊ ቀን ሲሳካና ኢትዮጵያ ዳግም የባህር በር ባለቤት ስትሆን ለማየት እንደሚመኙም በስሜት ገልጸዋል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ
#EBC #Ethiopia #Assab #Kombolcha #RedSea #HistoricalMemory #Hope #SeaAccess