የሀገራችንን የኢንዱስትሪ ልማት ለማቀላጠፍና በዘርፉ የሚታዩ የካፒታል እጥረት፣ የግብዓት አቅርቦትና የባለሙያ እጥረት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል አዲስ መመሪያ ይፋ መደረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር ገለጸ።
ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ መሠረት፣ በኢንዱስትሪ ልማት ውስጥ የሚታዩ ማነቆዎችን ደረጃ በደረጃ ለማቃለልና የሀገር ውስጥ ምርታማነትን ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን፣ በተለይም አስመጪዎች ምርቶችን ለገበያ ከማቅረባቸው በፊት የሚከፍሉት ቀረጥና ታክስ ውስን የሆነውን ካፒታላቸውን በመያዝ በስራቸው ላይ ጫና እንዳይፈጥር ታሳቢ ተደርጓል።
ይህንኑ ችግር ለመቅረፍ አስመጪዎች ግብዓቶችንና ምርቶችን ቀረጥና ታክስ ሳይከፍሉ ወደ ሀገር አስገብተው፣ ለምርቶቻቸው ገበያ ባገኙ ጊዜ ክፍያውን የሚፈጽሙበት የነጻ ንግድ ቀጣና አሰራር በየአካባቢው ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል።
እነዚህ ነጻ የንግድ ቀጠናዎች ባለሃብቶችን የበለጠ የሚሰቡ እንዲሆኑ ለማድረግ ከላይ ከተገለጸው በተጨማሪ በነጻ የንግድ ቀጠናዎች ውስጥ ተሰማርተው ግብአቶችን እና ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ ስራ ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች ከገቢ ግብር ነጻ እንዲሆኑ ተፈቅዷል።
ይህ ከገቢ ግብር ነጻ መሆን ባለሀብቶች ያላቸውን አቅም በሙሉ ተጠቅመው በንግድና በኢንዱስትሪው ዘርፍ እንዲሳተፉ የሚያበረታታ መሆኑን የጠቀሰው ሚኒስቴሩ፣ ባለሀብቶች የተፈቀደላቸውን ይህን ልዩ ዕድል በመጠቀም በነጻ የንግድ ቀጣናዎች ውስጥ በስፋት እንዲሰማሩ ጥሪውን አስተላልፏል።