ባለፉት 48 ሰዓታት በመካከለኛው ምሥራቅ የታየው ድንገተኛና ፈጣን ወታደራዊ ለውጥ፣ የዓለምን ጂኦ-ፖለቲካዊ ሚዛን ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግሮታል።
በኢራን፣ በእስራኤል እና በአሜሪካ መካከል ተከስቶ የነበረው ከፍተኛ ውጥረት፣ በፓኪስታን አደራዳሪነት ለሁለት ሳምንታት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርሷል። ይህም ለዓለምን የሰላም ተስፋ ጭላንጭል ሰጥቶ የናረውን ስጋት ለጊዜውም ቢሆን ጋብ አድርጎታል።
ይህ ፈተና የበለጠ የሚጎዳቸው እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አዳጊ ሀገራትን መሆኑን በተግባር ተገልጧል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ከዓመታት በፊት ቀድማ የነደፈቻቸው ስልታዊ የዲፕሎማሲ መንገዶች እና ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል ያደረጉ ፖሊሲዎቿ ዛሬ ላይ ለደረሱት ፈተናዎች እንዴት ፍቱን ምላሽ መስጠት እንደሚቻሉ በተግባር አሳይታለች።
አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ "ኦፕሬሽን ኤፒክ ፉሪ" የተሰኘውን መጠነ-ሰፊ የአየር ጥቃት ከጀመሩ በኋላ፣ ቀጣናው ወዴት እንደሚያመራ መተንበይ የብዙዎች ጭንቀት ሆኖ ቀይቷል። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቀነ ገደብ የተቀመጠ ዛቻ ደግሞ የጦርነቱን ሂደት እንቆቅልሽ አድርጎት ነበር። ይሁን እንጂ የሰዓት ገደቡ ከማለፉ በፊት በፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሸህባዝ ሻሪፍ አደራዳሪነት የተደረሰው ስምምነት፣ የሆርሙዝ የባሕር ሰርጥ ለንግድ መርከቦች ክፍት እንዲሆን አስችሏል።
ኢራን ወታደራዊ ግቦቿን ማሳካቷን በመጥቀስ ስምምነቱን ተቀብላለች። የዓለም የነዳጅ ገበያ እና የትራንስፖርት ዘርፍም ከፍተኛ እፎይታ እና ተስፋ አግኝቷል። በተለይም በቀይ ባሕር በኩል የሚደረገው የንግድ ፍሰት ዳግም መነቃቃቱ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለተፈጠረው የዋጋ ግሽበት ማስታገሻ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ይህ ሂደት ዓለም ወደ "ባለብዙ-ዋልታ" ሥርዓት እየተሸጋገረች መሆኗን እና የብሪክስ አባል ሀገራት እያሳደሩት ያለው ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑን በግልጽ ያሳየ ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል።
የኢትዮጵያ ስልታዊ መንገድ፡ ከጥገኝነት ወደ ሉዓላዊ ከፍታ
ይህ በመካከለኛው ምሥራቅ የታየው ክስተት ኢትዮጵያ የምትከተለውን "ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል ያደረገ ዲፕሎማሲ" አስፈላጊነት በድጋሚ አረጋግጧል። ሀገራችን በሌሎች ኃያላን ሽኩቻ ውስጥ ወገንተኛ ሳትሆን፣ የገነባችው ሉዓላዊ ዲፕሎማሲ ዛሬ ላይ በግርማ ሞገስ እንድትቆም አድርጓታል።
ኢትዮጵያ ቀድማ የጀመረችው የባሕር ኃይል ግንባታ እና "ወደ ባሕር የመጠጋት" ስትራቴጂካዊ ፍላጎት፣ የፖለቲካ ፍጆታ ሳይሆን የሀገራዊ ደኅንነት እና የኢኮኖሚ ነፃነት ዋስትና መሆኑን የሰሞኑ የቀይ ባሕር ውጥረት በቂ ማስረጃ ነው።
ያለ ኢትዮጵያ ንቁ ተሳትፎ እና ባለቤትነት፣ የቀይ ባሕር እና የምሥራቅ አፍሪካ ሰላም አስተማማኝ ሊሆን እንደማይችልም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እየተረዳው መጥቷል።
ዛሬ ኢትዮጵያ በብሪክስ አባልነቷ እና በአፍሪካ ሕብረት ውስጥ ባላት መሪ ሚና፣ በቀጣናው ጉዳይ ላይ ድምፅዋ የሚሰማ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገር ሆናለች።
መንግሥት የጀመራቸው የወደብ አማራጭ ስምምነቶች እና የዲፕሎማሲ ጥረቶች፣ ሀገራችን ከማንኛውም ወገንተኛ ጥገኝነት ነፃ ሆና ብሔራዊ ጥቅሟን እንድታስከብር ዕድል ፈጥረውላታል።
መካከለኛው ምሥራቅ አለመረጋጋት ለዓለም ፈተና ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ግን ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር በዲፕሎማሲያዊ ድል እና በኢኮኖሚያዊ ከፍታ ጉዞዋን ቀጥላለች።
ኢትዮጵያ ዛሬም ነገም የቀጠናው የሰላምና የብልጽግና የማይናወጥ ዋልታ ሆና ትዘልቃለች!
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ