ኢትዮጵያ እና ጃፓን ከ100 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ እና በታሪክ ፈተናዎች ውስጥ ያለፈ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አላቸው።
የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በይፋ የተጀመረው እ.አ.አ በ1930 የወዳጅነት እና የንግድ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ከጃፓን ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመመሥረት የመጀመሪያዋ የአፍሪካ አገር የመሆን ታሪካዊ ክብር አላት።
በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ እንደ ከበደ ሚካኤል ያሉ ኢትዮጵያውያን ምሁራን የጃፓንን የሥልጣኔ ጉዞ ለኢትዮጵያ እንደ አርዓያ በመመልከት “ጃፓን እንደምን ሰለጠነች?” በሚሉ ስልታዊ ሥራዎቻቸው የሁለቱን ሀገራት ምሁራዊ እና ባህላዊ ትስስር አጠናክረውታል።
የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሕገ-መንግሥትም የጃፓኑ የሜይጂ ሕገ-መንግሥት ልምድ የተወሰደበት ነበር። ይህም “ጃፓናውያን” ተብለው ይጠሩ የነበሩት የኢትዮጵያ ለውጥ ፈላጊ ምሁራን የጃፓንን ፈጣን የኢንዱስትሪ ሽግግር ለኢትዮጵያ ዕድገት እንደ መፍትሔ ይወስዱት እንደነበር ያሳያል።
ወደ ትብብር ያደገው የሀገራቱ ግንኙነት
የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ አማካሪ ኦው ሳዳማና እና የጃፓን ከፍተኛ የፓርላማ ልዑክ በኢትዮጵያ እያደረጉት ያለው ጉብኝት ለዚህ የቆየ ወዳጅነት አዲስ ስትራቴጂያዊ ምዕራፍ ከፍቷል።
የጃፓን መንግሥት ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን እንቅስቃሴ በይፋ እንደሚደግፍ ኦው ሳዳማና አስተውቀዋል። ይህም ለኢትዮጵያ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ትርጉም አለው።
ጃፓን የኢትዮጵያን የባሕር በር ፍላጎት እንደ ቅንጦት ሳይሆን ከ130 ሚሊዮን በላይ ለሆነው ሕዝብ የኢኮኖሚ ዕድገት እና ለቀጣናዊ ትስስር እጅግ አስፈላጊ የሆነ ብሔራዊ ግብ መሆኑን ተቀብላለች። ይህ የጃፓን ይፋዊ ድጋፍ ኢትዮጵያ ለጀመረችው የባሕር በር ተደራሽነት ጥያቄ ዓለም አቀፋዊ ሕጋዊነትን እና ዲፕሎማሲያዊ ክብደትን የሚጨምር ነው።
የጃፓን ድጋፍ ከኢኮኖሚ አጋርነት ባለፈ ሰፊ የደኅንነት ትብብርን ያካተተ ነው። ሁለቱ ሀገራት በሳይበር ደኅንነት፣ በሽብር መከላከል እና በድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዙሪያ ያላቸውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ተስማምተዋል። ይህም ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ያላትን ስትራቴጂያዊ ተፅዕኖ ጃፓን እንደምትገነዘብ ማሳያ ነው።
ስምምነቱ ጃፓን የምታራምደው “ነፃ እና ክፍት የኢንዶ-ፓስፊክ” ስትራቴጂ አካል ሲሆን፣ ዓላማውም በቀይ ባሕር እና በሕንድ ውቅያኖስ ቀጣና የሕግ የበላይነትን እና የመርከብ ጉዞ ነፃነትን ማረጋገጥ ነው።
ጃፓን ለኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ እውቅና መስጠቷ ኢትዮጵያ በዚህ ቁልፍ የባሕር መተላለፊያ መስመር ላይ ሚዛናዊ እና የተረጋጋ ሚና እንዲኖራት ፍላጎት እንዳላት ያሳያል። በተጨማሪም የባሕር ደኅንነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የኢትዮጵያ አቅም እሴት መሆኑን ማሳያ ነው።
የጃፓን መንግሥት የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ መደገፉ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ጥልቅ ታሪካዊ ወዳጅነት ወደ ስትራቴጂያዊ አጋርነት የቀየረ ሲሆን፣ ለኢትዮጵያም በቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች ላይ ያላትን ተሰሚነት ከፍ የሚያደርግ ነው።
በሌላ በኩል፣ የጃፓን ልዑክ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የሪፎርም ሥራ እና የከተማ ልማት ውጤቶች “ለሌሎች ሀገራት አብነት የሚሆን ነው” በማለት አድናቆቱን ገልጿል።
ይህም ከኢንዱስትሪ ፖሊሲ፣ ከካይዘን እና ከልማት ትብብር ባለፈ ጃፓን በኢትዮጵያ የሚታየውን ሀገራዊ ለውጥ እንደምትደግፍ ማሳያ ነው።
በለሚ ታደሰ
#Ethiopia #Japan #diplomacy #seaaccess #RedSea #geopolitics #maritimestrategy