Search

"ያደኩባት ፒያሳ እስክጠፋኝ ድረስ እጅግ ተለውጣ ጠብቃኛለች"

ሰኞ ሚያዝያ 05, 2018 44

ለረጅም ጊዜ በማረሚያ ቤት ቆይታ የነበራትና በትውልድ ሰፈሯ ፒያሳ ተወልዳ ያደገችው ቃልኪዳን፣ ከእስር ከተፈታች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ መልክ የተገነባችውን ፒያሳን ስትጎበኝ የታዘበችው ውበትና ለውጥ እጅግ አስገራሚ ሆኖባታል።

ቃልኪዳን የሰፈሩ ለውጥ እጅግ ማራኪ ከመሆኑ የተነሳ መንገዶች እንደጠፉባትና የምታውቃት ፒያሳ መሆኗን ለማመን እስኪያዳግታት ድረስ እጅግ ተለውጣ እንዳገኘቻት ተናግራለች።

ቀድሞ የነበሩት ጠባብ መንገዶችና ምቹ ያልሆኑ የመኖሪያ ቤቶች ዛሬ ውብ በሆኑ ፋውንቴኖች፣ ማራኪ ዲኮሮችና ሰፋፊ መንገዶች መተካታቸውን በአድናቆት ገልጻለች።

በተለይም "ሠራተኛ ሰፈር" ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የነበረው ወከባ ጠፍቶ፣ አካባቢው ጽዱና ዘመናዊ መልክ መላበሱ ትልቅ ለውጥ መሆኑን ጠቁማለች።

የፒያሳ በአዲስ መልክ መገንባትና የእሷ ከእስር ተፈትታ አዲስ ሕይወት መጀመር በአጋጣሚ መገጣጠሙን የጠቀሰችው ቃልኪዳን፣ "እኔም እንደ አዲሷ ፒያሳ አዲሷ ቃልኪዳን ሆኛለሁ" ስትል የውስጥ ለውጧንና ተስፋዋን አጋርታለች።

ምንም እንኳ ነዋሪዎች ከቦታው መነሳታቸው ቢታወቅም፣ ለሀገር ልማት ሲባል የተከናወነው ተግባር ለከተማዋ አዲስ ገጽታ መስጠቱንና ከነዋሪዎች ጋር ባሉበት ቦታ ግንኙነቱ እንደሚቀጥል ያላትን እምነት ገልፃለች።

የቃልኪዳን ታሪክ የከተማዋ ገጽታ መቀየር ብቻ ሳይሆን፣ የግለሰቦችን የሕይወት ለውጥና ዳግም የመወለድ ተስፋ አብሮ የሚያሳይ ሁነት ሆኗል።

በቢታንያ ሲሳይ

#EBC #Ethiopia #AddisAbaba #Piazza #CityTransformation #Hope #NewBeginnings