Search

ጆሞ ኬንያታ - አይረሴው የፓን አፍሪካኒዝም ዕሳቤ አራማጅ

ማክሰኞ የካቲት 03, 2018 36

 

“ልጆቻችን ስለ ቀድሞዎቹ ጀግኖች ሊማሩ ይችላሉ፤ የእኛ ተግባር ግን ራሳችንን የወደፊት አርክቴክቶች (አርቃቂዎች) ማድረግ ነው” በሚለው ታሪካዊ ንግግራቸው ይታወቃሉ - ጆሞ ኬንያታ።

የ“ማው ማው” አመፅን መርተዋል በሚል በብሪታንያ የቅኝ አገዛዝ ባለሥልጣናት ተከሰው ለዘጠኝ ዓመታት የታሰሩት ጆሞ ኬንያታ ከእስር ሲፈቱ “ካኑ” የተሰኘውን የኬንያ፣ አፍሪካን ብሔራዊ ሕብረት መርተው በምርጫ በማሸነፍ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ በመቀጠልም የመጀመሪያው የኬንያ ፕሬዚዳንት ሆነዋል

የ’ሃራምቤ’ ትብብር መንፈስ

ኬንያታ ስልጣን ሲይዙ ያስተዋወቁት ትልቁ ፍልስፍና ’ሃራምቤ’ የሚል ነበር። በስዋሂሊ ቋንቋ ‘ሁላችንም በጋራ እንተባበር/እንስራ የሚል ትርጉም ያለው ይህ ጽንሰ-ሀሳብ በኬንያ ብቻ የተገደበ አልነበረም።

ኬንያታ ይህንን የጋራ ትብብር ፍልስፍና ለአፍሪካ አንድነትም እንደ መፍትሔ አመላክተዋል። አፍሪካውያን በኢኮኖሚና በፖለቲካ ነፃነታቸውን ለማረጋገጥ ሃራምቤን በአህጉር ደረጃ መተግበር እንዳለባቸውም ያስረዱ ነበር።

ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት (OAU) ያበረከቱት ሚና

 የጆሞ ኬንያታ ስም ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት (ከአሁኑ አፍሪካ ሕብረት) ምስረታ ጋር በእጅጉ የተሳሰረ ነው። እ.አ.አ. በ1963 አዲስ አበባ ላይ የድርጅቱ ቻርተር ሲፈረም ኬንያታ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ነበሩ።

 የፓን-አፍሪካኒዝም ሃሳቦች መጋቢ በመሆን ፣ በቀጣናው ግጭቶች እንዲረግቡ በማድረግና የኢኮኖሚና የፖለቲካ ትብብሮችን በመፍጠር ለአህጉሪቱ አንድነት አበክረው መስራታቸውን ታሪክ ያስረዳል።

የፓን-አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ የነበሩት ጆሞ ኬንያታ በወቅቱ በአፍሪካ ሀገራት መካከል ለሚነሱ ግጭቶች (ለምሳሌ በኮንጎ ቀውስ ወቅት) የሰላም ድርድርን በመምራት "የአፍሪካ ችግር በአፍሪካውያን መፈታት አለበት" የሚለውን መርህ በተግባር አሳይተዋል።

ኬንያታ ለምስራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ (EAC) መመስረት ቁልፍ ሚና በመጫወት፣ ቀጣናዊ ትብብር ለአህጉራዊ አንድነት መሰረት መሆኑን አረጋግጠዋል።

የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አባት የሆኑት ጆሞ ኬንያታ እ.ኤ.አ. በ1978 ከዚህ ዓለም በሞት ቢለዩም፣ ለኬንያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ ትልቅ የታሪክ ዐሻራ ጥለው አልፈዋል።

በዚህም የተነሳ የአፍሪካ ሕብረት አባት ከሚባሉ መሪዎች ተርታ ስማቸው በጉልህ ይጠቀሳል።

ዛሬም ቢሆን የአፍሪካ ሕብረት “አንድ አህጉር፣ አንድ ሕዝብ” በሚል መሪ ቃል ለሚያደርገው ጉዞ፣ የኬንያታ የ“ሃራምቤ” መንፈስ እና የጥንካሬ ታሪክ እንደ ትልቅ ስንቅ ያገለግላል።

በጌትነት ተስፋማርያም

#EthiopianBroadcastingCorporation #JomoKenyatta #Harambee #PanAfricanism #AU