Search

አፍሪካ ችግሮቿን በራሷ በመፍታት ታላቅነቷን ታረጋግጣለች፡- ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)

ረቡዕ የካቲት 04, 2018 103

በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው 48ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ለአህጉሪቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ወሳኝ የሆኑ ነጥቦችን ያካተተ ንግግር አድርገዋል።
ሚኒስትሩ በንግግራቸው፤ የአፍሪካ ሕብረት ዋነኛ ዓላማ የአህጉሪቱን የኢኮኖሚ ነፃነት ማፋጠን ሊሆን እንደሚገባ ገልጸው፣ ለዚህም በጋራ ሰላምና በፖለቲካዊ ትብብር ላይ በቅንጅት መሥራት አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል።
አፍሪካ ለተባበሩት መንግሥታት (UN) ሪፎርም፣ ለዓለም አቀፍ ፋይናንስ ተቋማት ፍትሃዊነት እና ለአየር ንብረት ፍትህ በአንድ ድምፅ መቆም እንዳለባትም አስገንዝበዋል።
በአህጉሪቱ ስላለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ሲያብራሩም፤ በርካታ ሀገራት ሕብረቱ ምርጫቸውን እንዲታዘብላቸው መጠየቃቸው የሚበረታታ የጋራ እሴት እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰዋል።
ሆኖም ሕገ-መንግሥታዊ ባልሆኑ መንገዶች የሚደረጉ የሥልጣን ለውጦች የአህጉሪቱን ተሰሚነት ስለሚቀንሱ ሊወገዙ እንደሚገባ አስጠንቅቀዋል።
ኢትዮጵያ ለአህጉራዊ ትስስር ያላትን ቁርጠኝነት የገለጹት ዶ/ር ጌዲዮን፤ በተለይም የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠናን ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚደረገው ጥረት እንዲፋጠን ጥሪ አቅርበዋል።
ለዚህም እንደ ማሳያ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በኃይል እና በመሠረተ ልማት ዘርፍ የጀመረችው ትስስር ለአህጉሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር አስረድተዋል።
አፍሪካ እውነተኛ ለውጥ ከፈለገች ሕብረታችን እውነተኛ አንድነት ሊኖረው ይገባልያሉት ሚኒስትሩ፣ ይህ ጉባዔ በአህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ታሪካዊ ውሳኔዎችን ያሳልፋል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
በለሚ ታደሰ