አዲስ አበባ ዛሬ ላይ ስሟን የሚመጥን ታሪካዊና አስደናቂ ለውጥ ላይ ትገኛለች።
ከተመሰረተችበት የ19ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ ጀምሮ እስከ ዛሬው የኢትዮጵያ የብሪክስ (BRICS) አባልነት ዘመን ድረስ፣ አዲስ አበባ የሀገራችን ብቻ ሳትሆን የመላው አፍሪካ ኩራት እና የዲፕሎማሲ ማዕከል መሆኗን በተግባር እያረጋገጠች ነው።
በተለይም የ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ተሳታፊዎችን ለመቀበል ያደረገችው ዝግጅት ከተማዋን ወደ አዲስ የስኬት ምዕራፍ አሸጋግሯታል።

ከ130 በላይ ኤምባሲዎች፣ የአፍሪካ ሕብረት (AU)፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (UNECA) እና የአፍሪካ በሽታዎች መቆጣጠሪያ ማዕከል (Africa CDC) መገኛ የሆነችው መዲናችን፤ ከኒው ዮርክ እና ጄኔቫ ቀጥሎ የዓለም ትልቋ የዲፕሎማሲ ከተማ ሆና ትጠቀሳለች።
በከተማዋ የተከናወነው የኮሪደር ልማት መንገዶችን በማስፋት፣ የእግር መንገድ እና የብስክሌት መስመሮችን በማዘመን ከተማዋን ለዲፕሎማቶች እና ለእንግዶች ምቹና ማራኪ አድርጓታል።
በተጨማሪም በፒያሳ የሚገኘው የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ የሳይንስ ሙዚየም፣ እንዲሁም የአንድነት እና የእንጦጦ ፓርኮች የከተማዋን ሞራላዊ እና ባህላዊ ልዕልና ለዓለም እያስተዋወቁ ይገኛሉ።

በሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ ከ25 ሺህ በላይ ተሳታፊዎችን ያስተናገደችው አዲስ አበባ፤ አሁን ላይ ያላት የኮንፈረንስ አቅም እጅግ ከፍ ብሏል። ለዚህም የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ማስፋፊያ፣ የዲጂታል ቪዛ አገልግሎት እና እንደ ቴሌ ብር ያሉ ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓቶች ትልቅ አቅም ሆነዋል።
ዛሬ አዲስ አበባ በውበት ደምቃ፣ ሁለንተናዊ አቅሟን አሳድጋ የ39ኛውን የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ እንግዶችን መቀበል ጀምራለች።
ይህ ዝግጅት አዲስ አበባ እውነትም የአፍሪካ መዲና እና የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ማዕከል መሆኗን ዳግም የሚያረጋግጥ ታላቅ ስኬት ነው።
አዲስ አበባ ዛሬም እንደ ትናንቱ የአፍሪካ የነፃነት፣ የአንድነት እና የብልጽግና ተምሳሌት ሆና እንግዶቿን በደመቀ ሁኔታ እየተቀበለች ትገኛለች።
በለሚ ታደሰ
#Ethiopia #AddisAbaba #AUSummit #Diplomacy #LandOfOrigins