Search

ኢቢሲ - ከፓን አፍሪካኒዝም ተጋድሎ እስከ አህጉራዊ የሚዲያ ክብር ማማ

ሓሙስ የካቲት 05, 2018 115

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃነት እና አንድነት ተምሳሌት መሆኗ የአደባባይ ምሥጢር ነው። ይህንን ታሪካዊ ኃላፊነት ደግሞ በምሥል፣ በድምፅ እና በቃል ለዓለም በማስተጋባት ረገድ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ላለፉት ስድስት ዐሥርተ ዓመታት የአፍሪካ የበኩር ድምፅ በመሆን የማይተካ ሚና ተጫውቷል። 

በቅርቡ በአዲስ አበባ በተካሄደው የመጀመሪያው "የአፍሪካ ሚዲያ አዋርድ" ላይ ኢቢሲ ያገኘው ልዩ የክብር ሽልማትም ይህንኑ የቀደመ የአንበሳነት ሚናውን እና የወቅቱን የላቀ አበርክቶ የሚያረጋግጥ ሆኗል። 

የኢቢሲ (የቀድሞው የኢትዮጵያ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን) ታሪክ ከፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። እ.አ.አ በ1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአዲስ አበባ ሲመሠረት፣ ስብሰባውን እና የአፍሪካ መሪዎችን ድምፅ ለአህጉሪቱ ሕዝቦች በማድረስ ለአፍሪካ የነፃነት ታጋዮች የትግል አውድ ሆኖ አገልግሏል። 

ለአብነትም የደቡብ አፍሪካው ኤ.ኤን.ሲ (ANC) በአፓርታይድ ዘመን የኔልሰን ማንዴላ ፓርቲ የትግል መልዕክቶችን የሚያስተላልፍበት የ15 ደቂቃ የሬዲዮ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ሬዲዮ የአየር ሰዓት ይሰጠው ነበር።

የዚምባብዌው ዛኑ ፒኤፍ (ZANU PF) የሮበርት ሙጋቤ ንቅናቄም በተመሳሳይ መልኩ የአዲስ አበባን አየር በአማራጭነት በመጠቀም የነፃነት ጥሪውን ያስተላልፍ ነበር። 

ይህ ተግባር ኢቢሲን የመገናኛ ብዙኃን ተቋም ብቻ ሳይሆን፣ የአፍሪካውያን የነፃነት እና የበኩር ድምፅ ሆኖ የታላቅ ወንድምነት ሚና እንዲጫወት አድርጎታል።

ባለፈው ታኅሣሥ በአዲስ አበባ በድምቀት በተካሄደው የአፍሪካ ሚዲያ አዋርድ፣ ኢቢሲ እና ባለሙያዎቹ ደምቀው ታይተዋል። ይህ ሽልማት "ለጋራ ዓላማ፤ የሚተጋ የጋራ አህጉር" በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ ሲሆን፣ ከ40 በላይ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ 800 የሚሆኑ የሚዲያ ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል።

ኢቢሲ ለአፍሪካ አንድነት፣ ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ እና ለአህጉሪቱ ሁለንተናዊ ከፍታ ላበረከተው የረጅም ዘመን "ታሪካዊ እና ዘመን ተሻጋሪ" አስተዋፅኦው ልዩ እውቅና ተሰጥቶታል። 

ተቋሙ አፍሪካውያን በቅኝ ገዥዎች ላይ የተቀዳጇቸውን ታሪካዊ ድሎች እና የአፍሪካን ገናናነት በሚተርኩ ዘገባዎችን በመሥራቱ ልዩ ተሸላሚ ሆኗል።

የኢቢሲ የሽልማት ድል ትልቁ ትርጉም "የአፍሪካን ታሪክ በአፍሪካውያን አንደበት" የመተረክ ስኬት ነው። ለዘመናት በምዕራባውያን ሚዲያዎች የሚነገረው "የረሃብ እና የጦርነት" ትረካ ተቀይሮ፣ አህጉሪቱ ያሏትን የልማት ተስፋዎች፣ የባህል ሀብቶች እና የታሪክ ድሎች በራሷ ልጆች ድምፅ እንዲሰሙ በማድረግ ረገድ ኢቢሲ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።

ዛሬ ኢቢሲ በዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ታግዞ በ11 ቋንቋዎች መረጃዎችን በማሰራጨት የአጀንዳ 2063ን ግቦች እያሳለጠ ይገኛል። 

እንደ ‘ዶትስትሪም’ (DotStream) የመሰሉ አዳዲስ ዲጂታል መድረኮችም የአፍሪካን ድምፅ እስከ ዓለም ዳርቻ እንዲደርስ እያደረጉት ነው።

የኢቢሲ የአፍሪካ ሚዲያ አዋርድ ተሸላሚ መሆን የታሪክ አጋጣሚ ሳይሆን፣ የዓመታት ጥረት እና የፓን አፍሪካኒዝም ፅናት ውጤት ነው። ተቋሙ ከትናንቱ የነፃነት ትግል ድምፅነቱ ተነሥቶ፣ የዛሬው የአፍሪካ ብልፅግና እና አንድነት አቀንቃኝነቱ ድረስ ያለው ጉዞ በክብር መዝገብ ላይ ሰፍሯል። 

ኢቢሲ ዛሬም እንደ ትናንቱ "የአፍሪካ ድምፅ" ሆኖ መቀጠሉን ለዓለም አረጋግጧል።

አፍሪካውያን ትላንት ለነፃነታቸው አሁን ደግሞ ለሁለንተናዊ ብልፅግና እያደረጉት ያለውን የተቀናጀ ጥረት በምሥል፣ በድምፅ እና በቃል የአፍሪካ ድምፅ ሆኖ ለዓለም ማድረሱን ይቀጥላል።

 

በላሉ ኢታላ 

#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #Panafricanism #Africamediaaward #Africanarrative