ኢትዮጵያ ለጥቁር ሕዝቦች ነፃነትና ክብር የከፈለችው መስዋዕትነት በቃላት የሚገለጽ ስሜት ብቻ አይደለም፤ በመሬት ላይ የታተመ፣ በታሪክ አውድማ ላይ የደመቀ ሕያው እውነት እንጂ፡፡
ከዓድዋ ተራሮች የነፃነት ነጋሪት ጀምሮ እስከ ዘመናዊው ፀረ-አፓርታይድ ትግል ድረስ፤ አዲስ አበባ የጥቁር ሕዝቦች የክብር ካባ፣ የነፃነት እና የአንድነት መዲና ሆና ዘልቃለች።
የማሸነፍ ሥነ-ልቦና ስንቅ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ እንሚገልጸው፣ ኢትዮጵያ በ1888 ዓ.ም ወራሪውን የጣሊያን ጦር በዓድዋ ድል ስታደርግ፣ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ "የማሸነፍ ሥነ-ልቦናዊ የበላይነትን" በወርቃማ ቀለም ጽፋለች።
ይህ ድል አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ቀንበር ለመላቀቅ ላደረጉት ረጅም ጉዞ የማይነጥፍ የሞራል ስንቅ ሆኗቸዋል።
ኢትዮጵያ የፓን-አፍሪካዊነት መንፈስ መነሻ በመሆን፣ አህጉሪቱ ከእንግሊዝ፣ ከፈረንሳይ፣ ከፖርቹጋልና ከሌሎች ቅኝ ገዢዎች እግር ስር እንድትወጣ ፋና ወጊ ሆናለች።
እንደ እነ ኔልሰን ማንዴላ፣ ጆሞ ኬኒያታ እና ጁሊየስ ኔሬሬ ያሉ ታላላቅ መሪዎች በልዩ ልዩ ሥራዎቻቸው የኢትዮጵያዊነትን የነፃነት መንፈስ በመጥቀስ ሀገራቸውን ነፃ ለማውጣት ተጠቅመውበታል።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አህጉር ነፃነትና ክብር ያበረከተችው አስተዋጽኦ በስሜት ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን፣ በተጨባጭ መስዋዕትነት የተከፈለበት፣ ስልታዊና ዘርፈ ብዙ ድጋፍ የታየበት ነው።
በቀድሞው ዲፕሎማትና ጋዜጠኛ አምባሳደር ተፈራ ሻውል ዕይታ፤ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ እና በሥልጠና ድጋፍ በማድረግ፣ ለትግሉ ስንቅና ትጥቅ በማቅረብ፣ የአፍሪካ አንድነት እንዲጠናከር ትልቅ ሚና ተወጥታለች።
መሠረቱን አዲስ አበባ ያደረገው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አሁኑ የአፍሪካ ሕብረት) እስከ ዛሬ በመዝለቅ፣ የአህጉሪቱ በአንድነት የመቆም ነባራዊ እውነታን ያንጸባርቃል። "ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ" የመስጠት ፋና ወጊነቱንም በተግባር ቀጥሎበታል።
ኢትዮጵያ ትላንትም፣ ዛሬም ለጥቁር ሕዝቦች ሁሉ የኩራትና የነፃነት ተምሳሌት ሆና ትቀጥላለች።
በመሐመድ ፊጣሞ