Search

ቡሩንዲ የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ሰብሳቢነትን ተረከበች

ሓሙስ የካቲት 05, 2018 84

48ኛው የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ፣ ለ39ኛው የአህጉሪቱ መሪዎች ጉባኤ ስኬት መሠረት የሆኑ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ዛሬ ተጠናቋል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የአንጎላ ሪፐብሊክ የውጭ ግንኙነት ሚኒስትር እና የወቅቱ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ቴቴ አንቶኒዮ ባደረጉት ንግግር፤ ስብሰባው በአህጉራዊ ፋይዳ ባላቸው ጉዳዮች ላይ ውጤታማ መደምደሚያ ላይ መድረሱን ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ በቆይታው የኅብረቱን የሪፎርም ሂደቶች፣ ሹመቶችና የምርጫ ጉዳዮችን ጨምሮ ለቀጣዩ የመሪዎች ጉባኤ ዝግጅት ወሳኝ በሆኑ አጀንዳዎች ላይ በዝርዝር መክሮ ውሳኔ አሳልፏል።
ቴቴ አንቶኒዮ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽንና ቀጣናዊ መዋቅሮች የተላለፉ ውሳኔዎችን በተቀናጀና በወቅታዊነት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፤ ለአባል ሀገራትና ለቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማኅበረሰቦች ለነበራቸው ገንቢ ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በዕለቱ በተደረገው የሥልጣን ርክክብ ሥነ-ሥርዓት፣ የምክር ቤቱ ተረኛ ሰብሳቢነት ከአንጎላ ወደ ቡሩንዲ ሪፐብሊክ ተሸጋግሯል።
በዚህም መሠረት የቡሩንዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤድዋርድ ቢዚማና የቀጣዩ ተረኛ ሰብሳቢ ሆነው ተሰይመዋል።
ኅብረቱ መስራች መርሆዎቹን በመከተል ለአህጉራዊ ዘላቂ ሰላም፣ መረጋጋት፣ ውህደትና ልማት የሚሰራውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጽ ጉባኤው በስኬት ተጠናቋል።
በላሉ ኢታላ