Search

አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና ሊኖራት ይገባል - የአፍሪካ ኅብረት እና ተመድ

ዓርብ የካቲት 06, 2018 108

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማሕሙድ ዓሊ ዩሱፍ 39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፉ አዲስ አበባ ከገቡት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ (ሪፎርም) በአስቸኳይ መከናወን ያለበት ጉዳይ መሆኑን አንሥተው፣ በተለይ አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት የቀረበው ጥሪ በአስቸኳይ ሊተገበር የሚገባ ታሪካዊ ግዴታ መሆኑን ገልጸዋል።

በፍትሐዊነት፣ በርትዕ እና በባለብዙ ወገን ሥርዓቱ ተዓማኒነት ፍላጎት መሠረት፣ አፍሪካ በጋራ አቋሟ መሠረት በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና ሊኖራት እንደሚገባ በድጋሚ አረጋግጠዋል።

መሪዎቹ ከፀጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ ባለፈ፣ በአህጉሪቱ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የተወያዩ ሲሆን የኢንዱስትሪ መስፋፋት እና መዋቅራዊ ሽግግር አፅንኦት የሰጧቸው ጉዳዮች ናቸው።

የአፍሪካ ኢንዱስትሪ መስፋፋት ለአህጉሪቱ ዕድገት፣ ለወጣቱ ክብር ያለው የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለዘላቂ መረጋጋት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በአጀንዳ 2063 መሻቶች መሠረት ለመዋቅራዊ ሽግግር፣ ለምርቶች እሴት መጨመር እና ለጠንካራ ኢኮኖሚ ግንባታ ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

የተመድ ዋና ጸሐፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አፍሪካ ኅብረት ለተመድ "ስትራቴጂካዊው የባለብዙ ወገን አጋር" መሆኑን ገልጸዋል።

በሀብተሚካኤል ክፍሉ 

#AfricanUnion #UnitedNations #Agenda2063 #AntonioGuterres #AddisAbaba #Diplomacy