ኢትዮጵያ የዜጎችን ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረገ የዲጂታል መሠረተ ልማት ግንባታንና አህጉራዊ ትስስርን ለማጠናከር ስትራቴጂካዊ እርምጃዎችን እየወሰደች መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ስብሰባ ላይ ገልጸዋል።
ይህም በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ዕቅድ አማካኝነት የሀገሪቱን የቴክኖሎጂ ሽግግር ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግረው ነው የተናገሩት።
በዕቅዱ ስር የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ዜጎች አገልግሎቶችን በቀላሉ የሚያገኙበትን ምህዳር ለመፍጠር ያለሙ ናቸው።
በተለይም የ"ፋይዳ" ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያን ከዘመናዊ የክፍያ ሥርዓቶችና ከብሔራዊ የመረጃ ልውውጥ መድረክ ጋር በማገናኘት፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ቀልጣፋ የንግድ ግብይት እንዲኖር እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
ይህ አሰራር በዜጎችና በኩባንያዎች መካከል አመኔታን በመገንባት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ ያነቃቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ በኢትዮጵያዊው የመደመር ፍልስፍና ላይ የተመሠረተ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ዩኒቨርሲቲ ለመክፈት ዝግጅቷን ማጠናቀቋንም ይፋ አድርገዋል።
በመሠረተ ልማት ረገድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰዎችንና ገበያዎችን በማገናኘት ረገድ ግንባር ቀደም ሚናውን እየተወጣ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡
ይህንን ስኬት አህጉራዊ መሠረት ለማስያዝ አፍሪካን ከዓለም አቀፍ የንግድ ሰንሰለት ጋር የሚያስተሳስር ግዙፍና ዘመናዊ አውሮፕላን ማረፊያ በመገንባት ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም በስትራቴጂካዊ አጋርነት በመታገዝ በአፍሪካ ያለውን የዲጂታል ልዩነት ለመሙላት አገልግሎቱን ወደ ተለያዩ የአህጉሪቱ ሀገራት እያሰፋ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በመሐመድ ፊጣሞ