Search

ልዩነቶችን በውይይት እና በምክክር የመፍታት ባህልን ማዳበር ለዘላቂ ሰላምና ልማት ወሳኝ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ሓሙስ የካቲት 12, 2018 88

ችግሮችን በውይይት ፈትቶ ሰላምን በማስፈን ወደ ልማት ፊትን መመለስ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቄለም ወለጋ ዞን ያለውን የልማት እንቅስቃሴ በጎበኙበት ወቅት እንደገለጹት፣ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ በመፍታት እና ሰላምን በዘላቂነት በማስፈን ፊትን ወደ ልማት ማዞር ወቅቱ የሚጠይቀው አንገብጋቢ ተግባር ነው።

ወለጋ በተፈጥሮ ሀብት የታደለ ምድር በመሆኑ፣ እነዚህን ጸጋዎች ለሕዝብ ጥቅም ለማዋል ልዩነቶችን በሀገር ሽማግሌዎች እና በምክክር መፍታት ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል።

ሰላም ለማንኛውም ሀገራዊ ተግባር መነሻና መሠረት መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሕዝቡ ያለውን ጥልቅ የሰላም እሴትና በጎ ባህል ተጠቅሞ ችግሮቹን በራሱ እንዲፈታ አሳስበዋል።

ባለፉት ሦስት እና አራት ዐሥርት ዓመታት አካባቢው ሙሉ ሰላም ባለማግኘቱ ምክንያት ሕዝቡ ስለ ልማት በስፋት ለማሰብ እና ለማቀድ የነበረው ዕድል ጠባብ እንደነበርም አስታውሰዋል።

ይህም ማኅበረሰቡ ሊያገኝ የሚገባውን የልማት ተጠቃሚነት ወደኋላ እንዲጎተት ማድረጉን ጠቁመዋል።

"የዝሆንን አጥንት በዝሆን አጥንት ይሰብሩታል" የሚለውን ጥልቅ ብሂል በመጥቀስ፣ ሕዝቡን እርስ በርሱ በማጋጨት አካባቢው ሰላም እንዳያገኝ ሲደረግ የቆየውን ሴራ አጋልጠዋል።

ሕዝቡ በተፈጥሮ ጸጋው ተጠቅሞ ማደግ እና መልማት ሲገባው፣ የሰላም እጦት እና የመንቀሳቀስ ስጋት ትልቅ እንቅፋት እንደሆነበትም ነው ያብራሩት።

በመሆኑም ገንቢ ሐሳቦችን ወደ ተግባር በመለወጥ እና ተግዳሮቶችን በመቀነስ፣ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ሁሉም ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

በለሚ ታደሰ

#Ethiopia #PeaceThroughDialogue #WollegaDevelopment #AbiyAhmed #NationalUnity