የወለጋ ሕዝብ ተፈጥሮ የቸረውን ጸጋ በራሱ ጉልበትና በልጆቹ አመራር ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ገለጹ።
አቶ ጌታቸው በወለጋ በሁሉም ዞኖች ያደረጉትን ጉብኝት አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ አካባቢው ቀደም ሲል ከልማት ይልቅ ከፀጥታ ስጋት ጋር ተያይዞ ስሙ ይነሳ እንደነበር አስታውሰዋል።
ሆኖም አሁን ላይ የነበረው ሁኔታ ተቀይሮ እጅግ ተስፋ ሰጪ የልማት እንቅስቃሴዎችን መመልከታቸውን ተናግረዋል።
"ወለጋ ብዙ ጊዜ ስሙ ከልማት ይልቅ ከፀጥታ ችግር ጋር ጎልቶ የሚታወቅ፣ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መንቀሳቀስ አስቸጋሪ ተደርጎ የሚሳል አካባቢ ነበር። አሁን ግን እዚህ መጥተን ያየነው እንቅስቃሴ እጅግ ተስፋ ሰጪ ነው" ብለዋል አቶ ጌታቸው።
የወለጋ ተሞክሮ ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ጸጋ፣ ለውጥ ፈላጊ አመራር እና የአመራሩን መንገድ ተከትሎ የሚሄድ ሕዝብ ካለ አገሪቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ መለወጥ እንደሚቻል ማሳያ መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ሕዝቡ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ከማድነቅ ባለፈ፣ ሥራዎቹ ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ ከፍተኛ ቁርጠኝነት እያሳየ እንደሚገኝ በጉብኝታቸው መታዘባቸውን ጠቁመዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ አክለውም፣ የወለጋን አካባቢ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ እንደሚያውቁት ጠቅሰው፤ ቀደም ሲል "ሕግና ሥርዓት የሌለበት" ተደርጎ ይቆጠር የነበረው አመለካከት ተቀይሮ፣ አሁን ላይ አካባቢው ለተሻለ ዕድገትና ብልጽግና መሠረት እየጣለ መሆኑን በአንክሮ ገልጸዋል።
በመሐመድ ፊጣሞ