Search

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ 65ኛ ዓመት በዓል ሠራዊቱ ለላቀ አርበኝነት ራሱን የሚያዘጋጅበት ነው - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

ዓርብ የካቲት 13, 2018 97

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ 65 ዓመት በዓል ሠራዊቱ ለላቀ አርበኝነት ራሱን የሚያዘጋጅበት ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።

በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ 65 ዓመት የምሥረታ በዓል ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት በሐዋሳ ተካሂዷል። በመድረኩ ዕዙ ከምሥረታው ጀምሮ ያለፈበትን ጉዞ የሚተርክ መጽሐፍ ለምርቃት በቅቷል። 

የሀገር ሉዓላዊነትን በማስጠበቅ ተልዕኮዎችን በብቃት በመወጣት፣ ፈታኝ ሁኔታዎች የታለፉበት መንገድ በመጽሐፉ ተዳስሷል።

የዕዙ የተጋድሎ ታሪክ በተወሳበት በዚህ መጽሐፍ፣ ለሀገር የተከፈለ መሥዋዕትነት እና ደማቅ የተጋድሎ ታሪኮች ተካትተውበታል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ተጋድሎ ጸንታ ትኖራለችብለዋል።

የዕዙ 65 ዓመት በዓል ሲከበር ሠራዊቱ ለላቀ አርበኝነት ራሱን የሚያዘጋጅበት እንደሚሆንም አመልክተዋል።

የሠራዊቱ ታሪክ በጽሑፍ ተሰንዶ ለታሪክ እና ለትውልድ እንዲቀመጥ ጸሐፊያንን ማበረታታት እንደሚገባም ነው የተናገሩት። 

ዕዙ ላለፉት ዓመታት ሲጠቀምበት የቆየው አርማ በአዲስ ተተክቷል፤ በዚህም በመድረኩ የዕዙ አዲስ አርማ እንዲተዋወቅ ተደርጓል።

በሌላ በኩል ዕዙ በየጊዜው በትጥቅ ራሱን እያዘመነ የመጣበትን ሂደት የሚያሳዩ የጦር መሣሪያዎች ለዕይታ ቀርበው በታዳሚዎች ተጎብኝተዋል።

1953 . የተመሠረተው የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ፣ ሀገርን በጀግንነት በመጠበቅ ደማቅ የታሪክ አሻራ ያኖረ ዕዝ ነው።

ግዳጆችን በጀግንነት በመፈጸም በተሰማራባቸው ዐውደ ውጊያዎች ሁሉ ደማቅ ታሪክ ያለው የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ፣ 65 ዓመት የምሥረታ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ ይገኛል።

በፓናል ውይይቱ ላይ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት፣ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

በሚካኤል ገዙ

#EBC #Ethiopia #ENDF #SpecialOperationsCommand #65thAnniversary #NationalSecurity