Search

ለሕዝባችን መከታ፤ ለኢትዮጵያ ጠላቶች ደግሞ መቅሰፍት ነን - ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ

እሑድ የካቲት 15, 2018 88

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እና ለመንግሥት መከታ፣ ለጠላቶቿ ደግሞ መቅሰፍት ነው ሲሉ የዕዙ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ ገለጹ።
በሐዋሳ ከተማ እየተከበረ በሚገኘው የዕዙ 65ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ላይ ንግግር ያደረጉት ዋና አዛዡ፣ የኢትዮጵያ ጠላቶች ከጥፋት ድርጊታቸው የማይታቀቡ ከሆነ የሠራዊቱ ክንድ ብርቱ መሆኑን አስጠንቅቀዋል።
ጀግንነት የኢትዮጵያ ቀደምት የታሪክ አሻራ መሆኑን የጠቀሱት ሌተናል ጄኔራል ሹማ፣ የአሁኑ ሠራዊትም የቀደመውን ጀግንነት እና ወኔ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር አቀናጅቶ እየተገነባ መሆኑን በአሁኑ ወቅት እያሳየ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ከአንድ ሻምበል ተነሥቶ ዛሬ ለደረሰበት ከፍተኛ ደረጃ የበቃው፣ የሥልጠና አሰጣጡን በማዘመን እና ጠንካራ የሪፎርም ሥራዎችን በመተግበሩ መሆኑን አስታውቀዋል።
የዕዙ የቅበላ አቅም እና የሥልጠና ጥራት በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ደረጃ ማደጉን የገለጹት ዋና አዛዡ፣ ልዩ ኃይሉ በትንሽ መሥዋዕትነት ግዙፍ ግዳጆችን በድል መወጣት የሚችልበት ደረጃ ላይ መድረሱን አብራርተዋል።
እዙ ከምን ጊዜውም በላይ የተደራጀ፣ የተናበበ እና ጥራት ያለው መሆኑን ጠቁመው፤ በየብስ፣ በባሕርም ሆነ በማንኛውም የአየር ሁኔታ የተሰጠውን ግዳጅ በብቃት መፈጸም የሚያስችል አቅም እንዳለውም አረጋግጠዋል።
በአሁኑ ወቅትም እዙ ከመንግሥት እና ከሕዝብ የሚሰጠውን ማንኛውንም ግዳጅ ለመፈጸም በተሟላ ዝግጁነት እና በተጠንቀቅ ላይ እንደሚገኝ ሌተና ጄኔራል ሹማ አስታውቀዋል።
65ኛው የምሥረታ በዓል በልዩ ሁኔታ እንዲከበር የተፈለገው በዕዙ ላይ የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎችን ለማሳየት መሆኑን የጠቀሱት ጄኔራል መኮንኑ፣ ከበዓሉ ጋር ተያይዞም እዙን የሚመለከት አዲስ መጽሐፍ፣ የእዙን ኃይል የሚገልጽ ዓርማ እና ታሪኩን የሚዘክር ዘጋቢ ፊልም መዘጋጀቱን ይፋ አድርገዋል።
በለሚ ታደሰ