የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ 65ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በሀዋሳ ከተማ በደማቅ ወታደራዊ ሥነ-ሥርዓት እያከበረ ይገኛል።
ዕዙ በዚህ በዓሉ ላይ የ44ኛ ዙር ንጋት ኮርስ የኮማንዶ ሰልጣኞችን አስመርቋል።
በምርቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ፣ ለተመራቂዎቹ የቀይ መለዮ የመልበስ ፈቃድ የሰጡ ሲሆን፣ በስልጠናቸው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎችም መለዮ አልብሰዋል።

የዕዙ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ ባስተላለፉት የደስታ መግለጫ መልዕክት፣ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ከጊዜ ወደ ጊዜ በዘመናዊ ስልጠና እና በአካል ብቃት የጠነከረ የሰው ኃይል እያፈራ መሆኑን ገልጸዋል።
አዛዡ አክለውም፣ "እኛ ባለ ቀይ መለዮ ለባሾች ለጠላቶቻችን መቅሰፍት መሆናችንን ሁሉም ማወቅ አለበት። ኢትዮጵያን በማንም ተደፍራ የማታውቅና ነገም የማትደፈር ሀገር አድርገን የገነባናት በሕዝባችን አንድነትና የምድር ድሮን በሆኑት ጀግኖቻችን ደጀንነት ነው" ብለዋል።

ማንኛውም ኃይል ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመጣ የመከሩት ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ፤ አሻፈረኝ ካለ ግን እነዚህ ቀይ መለዮ ለባሾች በጦር ሜዳ ውሎ ማርሽ ቀያሪ መሆናቸውን በተግባር ያሳዩታል ብለዋል።
ተመራቂዎቹ በዚህ ታሪካዊ የ65ኛ ዓመት የምስረታ ቀን መመረቃቸው ትልቅ ክብር መሆኑ ገልጸው፣ ሀገርና ሕዝብ የጣለባቸውን ከፍተኛ አደራ በጀግንነትና በታማኝነት እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።