የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በ65ኛው የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የምሥረታ በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ከውስጥ እና ከውጭ የተሰነዘሩባትን ዘመነኛ ጥቃቶች በብቃት መክታ ወደ ላቀ ከፍታ መሸጋገሯን ገልጸዋል።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "እኛ ኢትዮጵያውያን የትልቅ ሕዝብ እና ሀገር ባለቤት ነን" በሚል ባስቀመጡት አቅጣጫ መሠረት መላው ሠራዊት በየክፍሉ በልዩ ሁኔታ ዘመናዊ ሆኖ እንዲደራጅ መደረጉን ገልጸዋል።
“በተለይም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተከፈተብንን ጦርነት በድል እየመከትን በተመሳሳይ ጊዜ የሠራዊቱን ግንባታ ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ መቻላችን በታሪካችን ልዩ ምዕራፍ የሚባል ስኬት ነው” ብለዋል ፊልድ ማርሻሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስቀመጡትን ታላቅ ሀገራዊ ዓላማ ለማሳካት ሠራዊቱ በ24 ሰዓት ንቃት እየሠራ ሲሆን፣ ሀገራዊነት እና የሀገር ትርጉም ያልገባቸው ባንዳዎች የሚያደርጉትን የትንኮሳ ሙከራ በብቃት በመመከት ሀገር የማፅናት ተልዕኮውን እያሳካ ይገኛል ሲሉም አክለዋል።
ሠራዊቱ በማንኛውም ሁኔታ እና ጊዜ የተሰጠውን ግዳጅ ለመወጣት ሙሉ ዝግጁነት እና ብቃት እንዳለው በልበሙሉነት አረጋግጠዋል።
ሠራዊታችን የንድፈ ሐሳብ ብቻ ሳይሆን የተግባር ሰው መሆኑን በተለያዩ ግንባሮች ያረጋገጠ ሲሆን፣ የሀገሪቱ የደኅንነት ዋስትና የሆነው የሪፐብሊካን ጋርድም ከዚሁ አንጋፋ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የወጣ መሆኑን በንግግራቸው ጠቅሰዋል።
የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ከ1953 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ፈተናዎችንና ውጣ ውረዶችን አልፎ ዛሬ ላይ እጅግ ጠንካራ መሰረት ላይ መገንባቱን የገለጹት ኢታማዦር ሹሙ፣ ይህ ኃይል በደርግ ዘመን፣ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት እንዲሁም በቅርቡ በሰሜኑ ጦርነት የማይታመኑ ጀግንነቶችን በመፈጸም ለሀገሩ ያለውን ታማኝነት በተግባር አስመስክሯል።
ለሚ ታደሰ