Search

“ሠራዊታችን በድሮን የመሰለል እና በካሚካዚ ምሽግን የማፈራረስ አቅም ያለው ነው” - የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

እሑድ የካቲት 15, 2018 164

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በድሮን የመሰለል እና በካሚካዚ ምሽግን የማፈራረስ አቅም ያለው ነው ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ይህ ኃይል ከሱማሌ ጫፍ እስከ ምጽዋ ጫፍ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የሽብር ጥቃቶችን የመከላከል እና የቀጠናውን ደኅንነት የማስጠበቅ ብቃት እንዳለውም አረጋግጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሐዋሳ በተካሄደው የ65ኛው የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የምሥረታ በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የሀገራችንን ሉዓላዊነት የሚያስከብር እና የአፍሪካን ሰላም የሚያረጋግጥ ዘመናዊ እና ብቁ የልዩ ኃይል (Elite Force) መገንባቱን አብስረዋል።
የአየር ወለድ ኃይሉን "የኢትዮጵያ ልዩ ስጦታ" ሲሉ የገለጹት ሲሆን፣ ሠራዊቱ ዓላማን እና ዲስፕሊንን አንግቦ ውጊያ የሚያስቀር እና የሚጨርስ ጀግና ነው” ብለዋል።
የመከላከያ ተቋሙ ተልዕኮ ራዕይ ያለው እና ለትውልድ የሚሻገር ተቋም መፍጠር መሆኑን ጠቅሰው፣ ሠራዊቱ ኢትዮጵያን የመገንባት፣ የመጠበቅ እና የማጽናት ታላቅ ኃላፊነት እንዳለበት አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ በልጆቿ መሥዋዕትነት አልተደፈረችም፣ ወደፊትም አትደፈርም፤ ሀገራችን በክብር እና በነጻነት ለልጆቿ የምትሸጋገር የአፍሪካ ፈርጥ ሆና ትቀጥላለች ሲሉ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ወታደራዊ ዝግጅት በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በድፍን አፍሪካ ሰላም እና ብልጽግናን ለማረጋገጥ እንዲሁም ለቀጣናው ሀገራት አለኝታ እና ጋሻ ለመሆን እንደሆነ ነው ገየለጹት።
ለዚህም ሲባል ቀደም ሲል በምድር እና በተራራ ላይ የነበረው ሥልጠና አሁን ወደ ባሕር መሸጋገሩን እና በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ ተቋም መገንባቱን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ የገነባችው ይህ ታላቅ ኃይል ዓለም አቀፍ ስምሪቶችን በብቃት የመወጣት እና የታሪክ ድርሻውን የመድገም ዝግጁነት እንዳለው ገልጸዋል።
የመከላከያ ኃይሉ የኢትዮጵያን ነፃነት እና የአፍሪካን ሰላም የሚያስከብር አስተማማኝ ጉልበት መሆኑን በመግለጽ፣ ለመላው የምሥራቅ አፍሪካ እና የአፍሪካ ሀገራት የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በዮናስ በድሉ