የሰው ልጅ ጥረትና ብርታት ማንኛውንም በረሃ ወደ ገነትነት የመቀየር አቅም እንዳለው የብላቴ አካባቢ ለውጥ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የብላቴ አካባቢ ልማትን በጎበኙበት ወቅት እንደተናገሩት፣ ከሦስት ዓመት በፊት በረሃ የነበረው ስፍራ ዛሬ በዘመናዊ መስኖ ለምቶ የሙዝ፣ የአቮካዶ እና የሃብሃብ ምርቶች የሚገኙበት ጥቅጥቅ ያለ "ጫካ" መምሰሉ እጅግ የሚያስደንቅ ነው።
በሲዳማ ክልል በ"ሌማት ትሩፋት" የተመዘገበው ውጤትም የዚሁ ስኬት አካል መሆኑን ጠቅሰው፣ የዶሮ ምርት ከጥቂት ሚሊዮኖች ተነስቶ ወደ 15 ሚሊዮን ማደጉ በምግብ ራሳችንን ለመቻል የምናደርገው ጥረት ፍሬ እያፈራ ስለመሆኑ ተጨባጭ ማሳያ ነው ብለዋል።
እነዚህ የግብርና፣ የኢንዱስትሪ እና የከተማ ልማት ሥራዎች በብቁ ተቋማት ታግዘው እና ተቀናጅተው ኢትዮጵያን ከድህነት እና ከልመና ታሪክ አውጥተው ብልፅግናን እንደሚያረጋግጡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በልበ ሙሉነት አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል በሐዋሳ ከተማ የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎችም የተፈጥሮ ውበትን ከሰው ሠራሽ ጥበብ ጋር በማዋሃድ ከተማዋን ለቱሪዝም ይበልጥ ሳቢና ምቹ እያደረጓት እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
ይህ የከተማ ግንባታ ከኢንዱስትሪ ዕድገት ጋር የተቆራኘ መሆኑን ጠቅሰው፣ በሚቀጥለው ዓመት ከሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከሶላር ምርቶች ብቻ ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት መታቀዱን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ከአዲስ አበባ ሐዋሳ ያለውን የጉዞ ጊዜ ወደ ሁለት ሰዓት ዝቅ የሚያደርገው የፈጣን መንገድ መጠናቀቅ የንግድ እና የቱሪዝም ትስስሩን ይበልጥ እንደሚያቀላጥፈው ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአካባቢውን ለውጥ ውጤታማነት ሲገልጹም፣ "የሰው ልጅ በርትቶ ከሠራ ምን ሊያመጣ እንደሚችል በተግባር አይተናል" በማለት በትጋት የሚመጣውን ለውጥ አድንቀዋል።
ለሚ ታደሰ