ዓለም አቀፍ ዝናን ያተረፈው ዩቲዩበሩ አይሾው ስፒድ (IShowSpeed) በኢትዮጵያ ቆይታው በታዘባቸው ነገሮች በጣም መገረሙን ለተከታዮቹ አጋርቷል።
ስፒድ በተለይ የአዲስ አበባን ዘመናዊ ገጽታ ሲመለከት፤ "የሥነ-ህንፃ ጥበባቸው እጅግ ዘመናዊና አፍሪካዊ ውበትን ያዋሃደ ነው፤ በጉዞዬ ካየኋቸው ሁሉ ምርጡን መሰረተ ልማት እዚህ አግኝቻለሁ" ሲል አድናቆቱን ችሯል።
የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠርም ሌላው የግርምት ምንጭ ሆኖታል። እርሱ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ላይ ሆኖ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር 2018 መሆኑን ሲያውቅም መገረሙን ተናግሯል።
"ወደ ኋላ በጊዜ የተጓዝኩ ያህል ነው የተሰማኝ፤ እንደ ህጻን ልጅ ደስ ብሎኛል" በማለት ስሜቱን ገልጿል። ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ያልተገዛች ሀገር መሆኗም "እጅግ አስገራሚ እውነታ" ሲል አሞካሽቶታል።
ለወትሮው ቡና የማይጠጣው ስፒድ፣ በቡና መገኛዋ ኢትዮጵያ ግን ሳይቀምስ አላለፈም። የኢትዮጵያ ቡና "ኃይል" ግን አልቀለደበትም።
ቡናውን እንደጠጣ በቀጥታ ስርጭቱ ላይ ሲጮህ፣ ሲገለባበጥና ከኢትዮጵያውያን ጋር ሲጨፍር አምሽቶ፣ በመጨረሻም ጉልበቱ አልቆ "በታሪኬ ለመጀመሪያ ጊዜ ራሴን ስቼ ወደቅሁ" ሲል የቡናውን አነቃቂነት መስክሯል። በኢትዮጵያ ያሳለፈው ጊዜም እጅግ ደማቅና የማይረሳ እንደነበር ስፒድ አረጋግጧል።
በላሉ ኢታላ