የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሠረት ስለ መራጮች ምዝገባ ማወቅ የሚገቡን ዋና ዋና ነጥቦች፦
መራጭ ለመሆን የሚፈለጉ መሠረታዊ መስፈርቶች
በአዋጁ አንቀጽ 18 መሠረት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በምዝገባው ዕለት ዕድሜው 18 ዓመት የሞላውና በምርጫ ክልሉ ቢያንስ ለስድስት ወራት የኖረ ከሆነ መመዝገብ ይችላል። ሆኖም በአዕምሮ ሕመም የመወሰን አቅም የሌለው መሆኑ የተረጋገጠበት ወይም የመምረጥ መብቱ በፍርድ ቤት የታገደ ሰው ለመመዝገብ ብቁ እንዳልሆነ በአንቀጽ 18(3) ላይ ተደንግጓል።
የምዝገባ ቦታ እና የጊዜ ሰሌዳ
ቦርዱ የምዝገባ ቀናትን ከምዝገባው 15 ቀናት በፊት ይፋ ማድረግ እንዳለበት በአንቀጽ 19 ተመልክቷል። ምዝገባ የሚከናወነው በየምርጫ ጣቢያዎች ብቻ ሲሆን ቤት ለቤት ምዝገባ የተከለከለ ነው። ሆኖም ለአርብቶ አደሮች እንደ አስፈላጊነቱ ተንቀሳቃሽ ጣቢያዎች ሊዘጋጁ እንደሚችሉ በአንቀጽ 20 ተደንግጓል።
ለማንነት ማረጋገጫ የሚያገለግሉ ሰነዶች
በአንቀጽ 21 መሠረት የቀበሌ መታወቂያ ወይም ፓስፖርት (ባይታደሱም) ዋና ሰነዶች ናቸው። እነዚህ ከሌሉ የመንጃ ፈቃድ፣ የመኖሪያ ምስክር ወረቀት ወይም የትምህርት መታወቂያ ያገለግላሉ። ምንም ዓይነት ሰነድ የሌለው ሰው በሦስት ምስክሮች ፊት መመዝገብ እንደሚችል አዋጁ ዕድል ሰጥቷል።
የመራጭነት ካርድ እና የምዝገባ ሥነ-ሥርዓት
አንድ መራጭ በአንድ ጣቢያ ብቻ መመዝገብ እንዳለበት በአንቀጽ 24 ሰፍሯል። ምዝገባው ሲጠናቀቅ ለድምፅ አሰጣጥ አስፈላጊ የሆነው የመራጭነት ካርድ ይሰጠዋል። ካርዱ ቢጠፋ ወይም ቢበላሽ የምዝገባው ጊዜ ሳይጠናቀቅ ለጣቢያው በማመልከት ምትክ ማግኘት ይቻላል።
የምዝገባ ግልጽነት እና ቅሬታ አቀራረብ
የምዝገባ መዝገብ ለሕዝብ ክፍት መሆን እንዳለበት በአንቀጽ 25 እና 27 ተደንግጓል። ማንኛውም ሰው በምዝገባው ሂደት ላይ ቅሬታ ካለው ለጣቢያው ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አቤቱታ ማቅረብ ይችላል። ያለ በቂ ሕጋዊ ምክንያት መራጩን ከመዝገብ መሰረዝ እንደማይቻል በአንቀጽ 28 ተጠቅሷል።
በለሚ ታደሰ
#Ebc #VoterRegistration #NEBE #Democracy #KnowYourRights #Proclamation1162 #VoterEducation