በሱዳን የኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ እና በተለምዶ "አርሚ 70" ተብለው የሚጠሩት የህወሓት ተዋጊ ኃይል የቀድሞ አባላት ወደ ሀገር ውስጥ በመግባት የተሀድሶ ሥልጠና መውሰድ ጀምረዋል።
ቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባላት የነበሩት እና በሰሜኑ ጦርነት ህወሓትን ደግፈው ሲዋጉ የቆዩት እነዚህ ከ500 በላይ የቀድሞ ተዋጊዎች ለፌዴራል መንግሥት ያቀረቡት የ‘ዲሞቢላይዜሽን’ ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቷል።
በዚህም መሠረት በአዋሽ አርባ ጊዜያዊ የ‘ዲሞቢላይዜሽን’ ማዕከል ሥልጠናቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን ሂደቱን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፣ የ"አርሚ 70" አባላት በፈቃደኝነት ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው የሂደቱ አካል መሆናቸው አዲስ የሰላም ተስፋን የፈነጠቀ መሆኑን ገልጸዋል።
ኮሚሽነሩ አክለውም እስካሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ85 ሺህ በላይ፣ በትግራይ ክልል ደግሞ ከ63 ሺህ በላይ የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለስ መቻሉን አስታውቀዋል።
የመከላከያ የሰው ሀብት ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ሃጫሉ ሸለመ በበኩላቸው፣ የቀድሞ ተዋጊዎቹ የመረጡት የሰላም መንገድ የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሌሎችም ይህንን ፈለግ በመከተል ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጡ እና ለሀገር ግንባታ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ሥልጠናውን ያጠናቀቁት የቀድሞ ተዋጊዎች በDDR (ትጥቅ መፍታት፣ ከውጊያ ማሰናበት እና መልሶ ማቀላቀል) ሂደት አልፈው በዘላቂነት ወደ ማኅበረሰቡ እንደሚቀላቀሉ ታውቋል።
በወንድወሰን አፈወርቅ
#PeaceProcess #DDR #NationalRehabilitationCommission #Tigray #Stability #PeaceBuilding