የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ከአሏቸው በርካታና ማራኪ የባሕል እሴቶች መካከል የሲዳማ ሕዝብ የእንግዳ አቀባበል ሥርዓት አንዱ ነው። በዚህ ሥርዓት ውስጥ የሚከናወኑት ‘ዳኤ ቡሹ፣ ቡሪሳሜ እና ቄጣላ’ ጥልቅ ማኅበራዊና ሞራላዊ ትርጉም አላቸው። እነዚህ እሴቶች ሲዳማዎች ለሰው ልጆች ያላቸውን ልዩ እና ጥልቅ ፍቅር የሚያሳዩ ናቸው።
ዳኤ ቡሹ
የሲዳማ ሕዝብ ለተከበረ እንግዳ የሚያቀርበው የመጀመሪያው የፍቅርና የትሕትና መግለጫ ሰላምታ ነው። "ዳኤ ቡሹ" የሚለው ቃል ቀጥተኛ ትርጉሙ "አፈር ይጫነኝ" ወይም "መሬቱ በእኔ ላይ ይሁን" ማለት ነው። ይህም ጋባዡ ለእንግዳው ያለውን ጥልቅ ክብርና መስዋዕትነትን ይገልጻል። እንግዳው ሊደርስበት የሚችለውን ማንኛውንም መከራ ወይም ችግር "እኔ ልቀበልልህ" የሚል የምኞትና የራስን ጥቅም የመተው ፍልስፍና የታከለበት ድንቅ የሰላምታ አሰጣጥ ነው። ዳኤ ቡሹ በዜማ ታጅበው የተከበረ እንግዳቸውን የሚቀበሉበት ነው።

ቄጣላ
ቄጣላ ለጀግኖችና ለክብር እንግዶች የሚከናወን የባሕል ጭፈራና ሽለላ ነው። ወንዶች ጦር (ኡርዴ) እና ጋሻ (ዎንቆ) በመያዝ በከፍተኛ ጉልበትና ወኔ ይጨፍሩታል። ይህ ባሕላዊ ክንውን እንግዳን ከማክበር ባለፈ፣ ማኅበረሰቡ የዓመቱን ክንውኖች የሚገመግምበት፣ ቅሬታዎችን የሚገልጽበትና ዴሞክራሲያዊ መብቱን የሚለማመድበት የሕዝብ መድረክ ሆኖ ያገለግላል።

ቡርሳሜ
ቡርሳሜ የሲዳማ ሕዝብ ዋነኛና የተከበረ የባሕል ምግብ ሲሆን፣ የሚዘጋጀው ከእንሰት (ዋሳ ወይም ቡላ)፣ ከወተትና ከገበታ ቅቤ ነው። በተለይ ለታላላቅ እንግዶችና በፊቼ ጫምባላላ በዓል ወቅት በልዩ ሁኔታ ለተከበሩ እንግዶች ይቀርባል። ምግቡ "ሻፌታ" በተባለ የሸክላ እቃ ላይ የሚቀርብ ሲሆን፣ የአንድነት፣ የብልፅግና እና የጋራ መረዳዳት ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል። ሲዳማዎች ዳኤ ቡሹ ብለው ለተቀበሉት የተከበረ እንግዳቸው ይህን ምርጥ ባህላዊ ምግብ በማቅረብ ፍቅራቸውን ይገልጻሉ።

እነዚህ እሴቶች የሲዳማ ሕዝብ ለእንግዳ ያለውን ክብር፣ ሰላምንና ማኅበራዊ ትስስርን የሚያንፀባርቁ የኢትዮጵያ ኩራት ናቸው።
በለሚ ታደሰ
#Sidama #Culture #FicheeChambalaalla #Burisame #Qetala #DaeBushu