በእስልምና አስተምህሮ ውስጥ በክብር እና በታላቅነት ወደር የማይገኝላት አንዲት ልዩ ሌሊት አለች። ይህች ሌሊት "ለይለቱል ቀድር" (የመወሰኛዋ ሌሊት) ትባላለች።
የዚህች ሌሊት ታሪክ እና አስፈላጊነት ከአምልኮ ምንዳ አልፎ ከሰው ልጅ ዕድሜ እና ከአላህ ፀጋ ጋር የተያያዘ ጥልቅ ምሥጢር አለው።
እንደ ሃይማኖቱ ምሁራን ገለጻ፣ ከነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በፊት የነበሩ ሕዝቦች (ለምሳሌ እንደ ነቢዩ ኑህ ሕዝቦች) በመቶዎች አልፎም በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታትን የመኖር ዕድል ነበራቸው።
ይህም ረጅም ዘመን አላህን ለማምለክ እና መልካም ሥራዎችን ለማከማቸት ሰፊ ዕድል ሰጥቷቸዋል።
በአንፃሩ የነቢዩ ሙሐመድ /ሰ.ዐ.ወ/ ተከታዮች አማካይ ዕድሜ ከ60 እስከ 70 ዓመት ብቻ ነው። ይህ አጭር ዕድሜ ከቀደሙት ሕዝቦች ጋር በምንዳ እንዳያወዳድራቸው ስጋት ቢፈጥርም፣ አላህ ለዚህ ሕዝብ ያለውን እዝነት ለመግለጽ ለይለቱል ቀድርን ሰጣቸው።
"በዚህች ሌሊት የሚከናወን አምልኮ ከሺህ ወራት (83 ዓመት ከ3 ወር) አምልኮ ይበልጣል" ይላሉ የእስልምና ሃይማኖት አባቶች።
ነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ሌሊቷን በረመዳን የመጨረሻዎቹ 10 ቀናት፣ በተለይም በጎደሎ ቁጥሮች (21, 23, 25, 27, 29) እንዲፈልጓት የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችን አዝዘዋል። ይህቺ ሌሊት የትኛዋ እንደሆነ በውል ባይታወቅም አብዛኞቹ ምሁራን 27ኛዋ ሌሊት እንደሆነች ይገልጻሉ።
እንደ ሃይማኖቱ ምሁራን ገለጻ ከሆነ ሌሊቷ በውል ተለይታ አለመታወቋ ሦስት ዋና ዋና ጥቅሞች አሉት። እነዚህም፦
ትጋትን ለመጨመር - ምዕመናን አንዲት ሌሊት ላይ ብቻ ተወስነው ሳይሆን ዐሥሩንም ሌሊት በጸሎት እንዲተጉ ያደርጋል።
ለረመዳን ክብር መስጠት - ወሩን በሙሉ በአምልኮ እንዲያሳልፉ መንገድ ይከፍታል።
የአላህ ምሥጢር - የሰው ልጅ ሁልጊዜም ከፈጣሪው ጋር ባለው ግንኙነት ንቁ እንዲሆን ይረዳዋል የሚሉ ናቸው።
ይህች ሌሊት "ልዩ" የምትባለው በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው፦
አንደኛ፣ የሰው ልጅ መመሪያ የሆነው ቅዱስ ቁርዓን ከሰማይ የወረደባት ሌሊት በመሆኗ።
ሁለተኛ፣ የሰው ልጆች ዓመታዊ ሲሳይ (ሪዝቅ)፣ ዕድሜ እና ሌሎች ጉዳዮች ውሳኔ የሚያገኙባት ሌሊት ነች።
በዚህች ልዩ ሌሊት ተራዊህ እና ተሀጁድ በትጋት መስገድ፤ ቁርዓን መቅራት፣ የበጎ አድራጎት ሥራ መሥራት፣ ዱዓ (ጸሎት) ማድረግ ከምዕመናን የሚጠበቁ ተግባራት ናቸው።
ለይለቱል ቀድር አጭር ዕድሜን በበረከት የምታረዝም፣ አማኝን ወደ ፈጣሪው የምታቀርብ እና የዓመቱን ዕጣ ፈንታ የምታቃና ታላቅ ስጦታ እንደሆነች የእስልምና የሃይማኖት አባቶች ይገልጻሉ።
ይህችን ሌሊት ማግኘት ማለት ሙሉ የሕይወት ዘመን አምልኮን እንደማግኘት ይቆጠራልም ይላሉ።