የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ170 ሚሊዮን ብር ወጪ በአዲስ አበባ ከተማ ኮተቤ አካባቢ ያስገነባውን ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኃይል መሙያ ጣቢያ ዛሬ በይፋ አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው እንደገለጹት፤ ተቋሙ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የኃይል መሙያ ጣቢያዎችን በስፋት በመገንባት ላይ ልዩ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል።
ዛሬ የተመረቀው የኃይል መሙያ ጣቢያ በቀን 24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸውን የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ የኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃቀም ባህልን ለማሻሻልና ከፍተኛ የኃይል ጭነት በማይኖርበት ወቅት ደንበኞች ኃይል እንዲጠቀሙ ለማበረታታት ምክንያታዊ የዋጋ ተመን ተፈጻሚ መደረጉን አስረድተዋል።
በትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በርኦ ሀሰን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሠራች መሆኑን ገልጸው፤ ሀገሪቱ ለነዳጅ ግዢ የምታወጣውን ከፍተኛ ወጪ ወደ ሌሎች ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ማዋል እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አጠቃቀም ረገድ ተጨባጭ ውጤት ማምጣቷን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ካለው ፍላጎት አንጻር ተጨማሪ የኃይል መሙያ ጣቢያዎችን ለመገንባት በዘርፉ ለሚሰማሩ የግል ባለሀብቶች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ140 ሺህ በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሲሆን፣ ለእነዚህ ተሽከርካሪዎች የሚመጥኑ የኃይል መሙያ ጣቢያዎች ግንባታም ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በመጀመሪያው ምዕራፍ በአዲስ አበባ 32፣ በሌሎች ከተሞች ደግሞ 8 በድምሩ 40 የኃይል መሙያ ጣቢያዎችን ለመገንባትና አገልግሎት ለማስጀመር በትኩረት እየሠራ መሆኑን አስታውቋል።
በተጨማሪም አገልግሎቱ በፒያሳ ኤሌክትሪክ ሕንፃ ግቢ ውስጥ ያስገነባውን የኃይል መሙያ ጣቢያ ዛሬውኑ ሥራ አስጀምሯል።
በአባዲ ወይናይ